Fana: At a Speed of Life!

በሲዳማ ክልል የኢትዮጵያ ታምርት 2ኛ ዙር ንቅናቄ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሲዳማ ክልል የኢትዮጵያ ታምርት 2ኛ ዙር ንቅናቄ መድረክ እየተካሄደ ነው፡፡
በመድረኩ የተገኙት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል÷በኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፎች ኢንዱስትሪ ካልተስፋፋ በስተቀር እድገትን ማምጣት ስለማይቻል ኢንዱስትሪዎችን ማስፋፋት የግድ ይለናል ብለዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ስራዎች ጊዜያዊ ባለመሆናቸው ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው ኢንዱስትሪዎችን በቀጣይነት ማስፋፋትና ማሰራት በሚቻልበት ላይ በትኩረት መስራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡
ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው÷የክልሉን ሃብቶች በሚገባ በመጠቀም ክልሉን የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ ወደ ስራ እንደተገባ ገልፀዋል።
ወደ ክልሉ የሚመጡ አዳዲስ ኢንዱስትሪዎችን ለመቀበል አስፈላጊ ሁኔታዎችን የማመቻቸትና የመደገፍ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቅሰዋል፡፡
በተጀመረው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በሲዳማ ክልል በተለያዩ ችግሮች ማምረት አቁመው የነበሩ 34 ኢንዱስትሪዎች በንቅናቄው መካተታቸውን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ሃላፊ አቶ አሻግሬ ጀምበሬ ናቸው፡፡
8 ኢንዱስትሪዎች ወደ ማምረት ስራ እንደገቡ ጠቅሰው÷ 11 ኢንዱስትሪዎች ደግሞ በመግባት ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር መሪነት የኢንዱስትሪ ምክር ቤት ተቋቁሞ በክልሉ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎችን የማንቀሳቀስ ስራም እየተከናወኑ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
በሲዳማ ክልል በተሰማሩ 1 ሺህ 54 ኢንዱስትሪዎች ከ60 ሺህ በላይ ዜጎች የስራ እድል እንደተፈጠረ ተገልጿል።
በቢቂላ ቱፋና ደብሪቱ በዛብህ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.