Fana: At a Speed of Life!

ቦርዱ በወላይታ ዞን ህዝበ ውሳኔ አፈፃፀም ላይ ተጨማሪ ምርመራ እንዲካሄድ አዘዘ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 13፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በወላይታ ዞን የተደረገው የሕዝበ ውሣኔ ሂደት ሕጋዊነት ለማረጋገጥ አዳጋች ሁኔታ በመፈጠሩ አፈፃፀም ላይ ተጨማሪ ምርመራ እንዲደረገ አዘዘ፡፡

ምርጫ ቦርድ በሒደቱ ቁጥራቸው ጥቂት በማይባል የምርጫ ጣቢያዎች በሕጉ መሠረትና  አግባብነት ባላቸው መመሪያዎች እንደ ከባድ የአሠራር ጥሠት የሚቆጠሩ ተግባራት መፈጸማቸውን ገልጿል፡፡

በመሆኑም  የጥሰቶቹን ስፋት እና የሚሸፍኗቸውን ጣቢያዎች በተመለከተ ቦርዱ ተጨማሪ ምርመራ እንዲከወን ማዘዙን ከቦርዱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

የምርመራ ሥራው እንደተጠናቀቀም የመጨረሻውን ውሣኔ በጉዳዩ ላይ እንደሚሰጥ  ነው ቦርዱ ያስታወቀው።

በዞኑ የህዝበ ውሳኔ አፈፃፀም ሒደት የታዩ ጥሠቶች ዝርዝር እንደሚከተለው ቀርቧል ፡-

  1. በመራጮች ምዝገባ ወቅት በመዝገቡ ላይ የሠፈረው የመራጮች ፊርማ በድምፅ መስጫ ቀን ከተፈረመው ፊርማቸው ጋር የተለያየ መሆን፣
  2. በምዝገባ ወቅት በጽሑፍ ፊርማ የተፈረመ በድምፅ መስጫ ቀን በጣት አሻራ የተፈረመ የመራጮች ዝርዝር በመዝገቦቹ ላይ መታየቱ፣
  3. በምዝገባ ወቅት በጣት አሻራ የተፈረመ በድምፅ መስጫ ቀን በጽሑፍ ፊርማ የተፈረመ የመራጮች ዝርዝር በመዝገቦች ላይ መታየቱ፣
  4. በመራጮች መዝገብ ላይ ለተመዘገቡ የተለያዩ መራጮች (በምዝገባ ወቅትም፣ በድምፅ መስጫ ቀንም) አንድ ዓይነት ፊርማ ተፈርሞ መገኘቱ፣
  5. በመራጮች መዝገብ ላይ ከሚጠበቀው በላይ ብዛት ያለው የጣት አሻራ ምልክት (በመራጮች ምዝገባ ወቅትና በድምፅ መስጫ ቀን) የተደረገ መሆኑ፣
  6. በመራጮች መዝገብ ላይ የመራጮቹ መረጃ ተሞልተው ፊርማቸው በጽሑፍም ሆነ በአሻራ አለመሥፈሩ፣
  7. ከ18-50 ዕድሜ ያላቸውና ማንበብና መጻፍ ይችላሉ ተብለው የሚገመቱ በርካታ መራጮች በአሻራ እንደፈረሙ መታየቱ፣
  8. በመራጮች ምዝገባ ቀን በአሻራ ተፈርሞ በድምፅ መስጫ ቀን ፊርማ መፈረም ባለበት ቦታ ላይ የራይት ምልክት መደረጉ፣
  9. በመራጮች መዝገብ ላይ ስለመራጮቹ ሊሠፍሩ የሚገቡ የመራጮች መረጃ በአግባቡ አለመሞላታቸው፤
  10. የድምፅ አሰጣጥና ውጤትን በተመለከተ
  11. ጥርጣሬን በሚፈጥር ሁኔታ በበርካታ ጣቢያዎች በመራጭነት የተመዘገቡና በሕዝበ ውሣኔው ቀን የመረጡ የመራጮች ብዛት ዕኩል ሆኖ መታየት፣
  12. የውጤት ማሳወቂያ ቅጽ ላይ የማይፈቀዱ የዕርምት ሥራዎች መሠራቱና በሠነዶቹ ላይ ከፍተኛ ሥርዝ ድልዝ መታየቱ፣
  13. የድምፅ መስጫ ወረቀት ብዛት፤ ከተመዘገቡና ድምፅ ከሰጡ መራጮችና ቁጥር አለመታረቅ፣
  14. የውጤት መግለጫ ቅጾችና የመራጮች መዝገብ ላይ ምርጫ አስፈጻሚዎች ፊርማቸውን በሠነዶቹ ላይ አለማሥፈራቸው፣
  15. ብዛት ያላቸው የድምፅ መስጫ ወረቀቶች በአንድ ላይ ታጥፈው በድምፅ መስጫ ሣጥን ውስጥ ታጭቀው መገኘታቸው፣
  16. በድምፅ መስጫ ቀን ድምፅ ለመስጠት ለተሠለፉ መራጮች ጊዜያዊ መታወቂያ ወረቀት በአካባቢ አሰተዳደር አካላት መታደል መሆናቸውን ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.