Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ የከባቢ አየር ብክለቱ እየጨመረ መሆኑ ተመለከተ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ የከባቢ አየር ብክለት መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የአዲስ አበባ ከተማ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ገለጸ፡፡
በየጊዜው የሚለካው የሙቀት አማቂ ጋዞች ወደ አካባቢ የሚለቀቀው መጠን በየሁለት ዓመቱ እንደሚተነተን ተገልጿል፡፡
ትንተናዎች እንዳመላከቱትም የአየር ጥራቱ  ሁኔታ እየቀነሰ ነው፡፡
በባለስልጣኑ የአማቂ ጋዞች ልኬት ቅነሳ እና ክትትል የአረንጓዴ ቴክኖሎጂ ማስፋፊያ ቡድን መሪ ሰሎሞን መለሰ እንደገለጹት÷ በመዲናዋ ያለው የሙቀት አማቂ ጋዝ መጠን ልኬት በፈረንጆቹ 2012 እና 2016 በተደረገው የልኬት ትንተና መሰረት ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመር አሳይቷል፡፡
በፈረንጆቹ የዘመን ቀመር በ2012 በተደረገ የልኬት ትንተና 4 ሚሊየን 888 ሺህ 677 ቶን ካርበንዳይ ኦክሳይድ እኩቨለንት (co2 e) እንዲሁም በ2016 የተከናወነው ትንተና እንዳመላከተው ደግሞ 14 ሚሊየን 479 ሺህ 132 ቶን ካርበንዳይ ኦክሳይድ እኩቨለንት (co2 e) ደርሷል፡፡
ለአየር ብክለት መጠኑ መጨመርም÷ የትራንስፖርት ዘርፉ፣ በቤት ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውሉ የኃይል አማራጮች እና የአደባባይ የቆሻሻ አወጋገድ በቅደም ተከተላቸው ተጽዕኖ ማሳደራቸውን አቶ ሰሎሞን ጠቅሰዋል፡፡
የአየር ብክለቱን ለመቆጣጠር ብሎም ለመቀነስ እንዲቻል ለብክለቱ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ተቋማት ተለይተው በጋራ እየተሠራ መሆኑን ነው አቶ ሰሎሞን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የተናገሩት፡፡
በዚሁ መሰረት÷ ከአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ፣ ከአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለስልጣን፣ ከጽዳትና ደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ፣ ከአዲስ አበባ የሥራ ዕድል ፈጠራ ኢንተርፕራይዝ፣ ከአዲስ አበባ ከተማ ግብርና ቢሮ፣ ከአዲስ አበባ የከተማ ውበት አረንጓዴ ልማት ቢሮ እና ከቤቶች ልማት አስተዳደር ጋር በጋራ እየሠራን ነው ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ያለውን የአየር ጥራት መጠን የሚያሳዩ 16 መሣሪያዎች መተከላቸውንም ነው የቡድን መሪው የተናገሩት፡፡
ሴክተሮች እና ማህበረሰቡ ሥራቸውን ሲያከናውኑ አየርን የማይበክሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በስፋት እንዲጠቀሙ ባለስልጣኑ ድጋፍ እና ክትትል እንደሚያደርግ ተጠቁሟል፡፡
በዮሐንስ ደርበው
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.