Fana: At a Speed of Life!

በቤኒሻንጉል ጉሙዝና ጋምቤላ ክልሎች በማዕድን ዘርፍ ንግድ ላይ ከፍተኛ አሻጥር መኖሩ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ጋምቤላ  ክልሎች የማዕድን ዘርፍ ልማት ላይ የንግድ አሻጥር ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ እንደሚገኝ ተገልጿል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ማዕድን ቢሮ ኃላፊ አቶ ካሚል አህመድ ÷ ክልሉ ባለፈው ዓመት 2 ሺህ 300 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ማቅረብ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ አሁን ላይ በሚስተዋለው የንግድ አሻጥር ምክንያት  ዝቅተኛ አፈጻጸም መመዝገቡን  ነው ያስረዱት፡፡

ችግሩን ለመቅረፍም በክልሉ ርዕሰ መስተዳደር የሚመራ የጸጥታ መዋቅር ተዋቅሮ የቁጥጥር ተግባር እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ  የጋምቤላ ክልል ማዕድን ቢሮ ÷ ወርቅን በአግባቡ ለማምረት እና ወደ ገበያ ለማቅረብ ህገወጥ የገበያ ሰንሰለቱ ችግር እየፈጠረ መሆኑን  አስታውቋል፡፡

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ኮንግ ሬት ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት ÷ ክልሉ ባለፈው ዓመት 1 ሺህ 200 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ገቢ አድርጓል፡፡

በተያዘው ዓመት ስድስት ወራት ግን 81 ነጥብ 5 ኪሎ ግራም ወርቅ ብቻ ለብሔራዊ ባንክ ገቢ መደረጉን ነው የተናገሩት፡፡

በዘርፉ የሚስተዋለውን ህገ ወጥነት ለመከላከልም በርዕሰ መስተዳድሩ የሚመራ የፀጥታ ግብረ ሃይል በማዋቀር እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ሃላፊው ጠቁመዋል፡፡

በክልሉ የወርቅ ምርትን ከማሳደግ በፊት ግብይቱን ጤናማ ማድረግ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ  እንደሚገኝም አብራርተዋል፡፡

በሰለሞን ይታየው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.