Fana: At a Speed of Life!

የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤት ይፋ መሆኑን ተከትሎ የተማሪዎች ውጤት በሚል የሚሰራጩ ሐሰተኛ መረጃዎች ነገር…

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰሞኑን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤት ይፋ መሆኑን ተከትሎ የተማሪዎች ውጤት በሚል ሐሰተኛ መረጃዎች እየወጡ ይገኛል።

አንዳንዶች ከፍ ያለ ውጤት እንዳገኙ የሚገልጽ ሐሰተኛ ማስረጃ ሲያዘጋጁ ሌሎች ደግሞ እጅግ ዝቅተኛ ውጤት እንዳገኙ በመግለጽ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ሐሰተኛ መረጃ እያዘዋወሩ ነው።

ለአብነትም ከ280 ሺህ በላይ ተከታይ ባለው አንድ የፌስ ቡክ ገፅ ላይ “አድማሱ አባተ ድንባለ” በሚል ስም የሚጠራ ግለሰብ በገሳ ዳላባ ትምህርት ቤት ተማሪ እንደሆነ በመግለጽ በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና 27 ነጥብ አምጥቻለሁ በሚል በማህበራዊ ሚዲያ የፎቶ መረጃ አሰራጭቷል።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ባደረገው ማጣራት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ውስጥ በሚገኘው ገሳ ዳላባ ትምህርት ቤት በግለሰቡ ስም የሚታወቅ ተማሪ የለም።

የሀገር አቀፍ ትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ግለሰቡ ከላይ የተገለጸው ትምህርት ቤት ተፈታኝ ያለመሆኑን አረጋግጧል።

በአገልግሎቱ የፈተናዎች አስተዳደር መሪ ስራ አስፈጻሚ የሆኑትን ወንድወሰን ኢየሱስወርቅ ዘነበ፤ ግለሰቡ የተጠቀመው መለያ ቁጥር ትምህርት ቤቱ የሚጠቀምበት መለያ ኮድ ውጭ እንደሆነ አመልክተዋል።

የት/ቤቱ መለያ ኮድ የሚያርፈው ከ2123014 እስከ 2123369 ሆኖ ሳለ ግለሰቡ የተጠቀመው መለያ ኮድ 2127154 መሆኑ በግለሰቡ የሀሰተኛ ፈተና ውጤት መግለጫ ላይ በግልጽ መታየቱ ሀሰተኛ መረጃ መሆኑን እንደሚረጋግጥ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደምም ትክክል ያልሆኑና ህብረተሰቡን የሚያወናብዱ መረጃዎችና መሰል ድርጊቶች ተከስተው እንደሚያውቁ ገልጸው፤ ህብረተሰቡ ለተሳሳቱ መረጃዎች ሰለባ እንዳይሆን ጥንቃቄ እንዲያደርግ መክረዋል፡፡

በተለይም አንዳንድ ተማሪዎች ለወላጆች ሐሰተኛ የውጤት መግለጫ በማቅረብ እያደናገሩ እንደሆነ መረጃዎች እየወጡ በመሆኑ ወላጆች የልጆቻቸውን ውጤት በአግባቡ ማጣራት እንዳለባቸው ፋና ማጣሪያ ያስገነዝባል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.