Fana: At a Speed of Life!

ከ345 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች ተያዙ

አዲስ አበባ ፣ ታኅሣስ 17 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጉምሩክ ኮሚሽን ከታህሳስ 5 እስከ ታህሳስ 11 ቀን 2016 ዓ.ም ባደረገው ክትትል ከ345 ሚሊየን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች ተይዘዋል፡፡

ኮሚሽኑ ባደረገው ክትትል 173 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የገቢ የኮንትሮባንድ እቃዎች እና 171 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር የወጪ፥ በድምሩ 345 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎች በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ተይዘዋል፡፡

ከተያዙት የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል አልባሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ መድሀኒት፣ የመዋቢያ እቃዎች፣ ጫት፣ አደንዛዥ እጾች፣ የመኪና መለዋወጫ፣ የምግብ ዘይት እና የተለያዩ ሀገር ገንዘቦች ይገኙበታል፡፡

በተጠቀሰው የጊዜ ገደብ የገቢ እና የወጪ ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ፣ አዋሽ እና ሞያሌ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ቀዳሚውን ስፍራ ሲይዙ በቅደም ተከተላቸውም 83 ሚሊየን፣ 64ሚሊየን እና 59 ሚሊየን ብር የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎችን መያዝ ተችሏል፡፡

የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ በጉምሩክ ኮሚሽን ሰራተኞች፣ በፌደራል ፖሊስ፣ በክልል ፖሊስ አባላትና ህብረተሰቡ ባደረጉት የጋራ ጥረት በፍተሻ፣ በበረራና በጥቆማ የተያዙ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ኮንትሮባንዱን ሲያዘዋውሩ የተገኙ 13 ተጠርጣሪዎች እና ስምንት ተሽከርካሪዎችም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የኮሚሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.