Fana: At a Speed of Life!

በዝቋላ ንጹሃን በመግደል የተሳተፉ የአሸባሪው ሸኔ 2 ሻምበሎች ከነ አዛዦቻቸው ተደመሰሱ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 2፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በዝቋላ አቦ ንጹሃን ካለርህራሄ በመግደል የተሳተፉ የአሸባሪው ሸኔ ሁለት ሻምበሎች ከነ ሻምበል አዛዦቻቸው መደምሰሳቸውን የጉና ክፍለ ጦር አራተኛ ሬጅመንት አስታወቀ፡፡

በምስራቅ ሸዋ ዞን ሊበን ጭቋላ ወረዳ አዋሽ ወንዝን ተከትሎ ባሉ ቀበሌዎች እና በዝቋላ አቦ ተራራማና ጫካማ አካባቢ ተሰግስጎ የሽብር ሴራ ሲፈፅም የነበረው አሸባሪ ሃይል ከጥቅም ውጭ መደረጉ ተገልጿል።

የክፍለ ጦሩ ምክትል አዛዥ ለኦፕሬሽናል ሌተናል ኮሎኔል ካሳሁን አማረ÷ የሽብር ቡድኑን ለማጥፋት መረጃ በመሰብሰብ እና በማጥናት እልህ አስጨራሽ ክትትል መደረጉን ተናግረዋል፡፡

ቡድኑ በዋለበት የማያድር፣ ባደረበትም የማይውል መሆኑ ለግዳጅ አስቸጋሪ እንደነበር ጠቁመው÷ ሠራዊቱ የጠላትን ስልት በማወቁና ጠላትን ለመምታት ካለው ቁርጠኝነት አንፃር በገባበት እየገባ መደምሰሱን ገልጸዋል።

መቶ አለቃ ደምስ ተሾመ በበኩላቸው÷ በአካባቢው ተሰግስጎ የነበረው ጠላት አሰቃቂ የሽብር ሥራ ሲፈጽም እንደነበር አስረድተዋል፡፡

ከመዝረፍና ከማገት ሌላ በዝቋላ አቦ ንፁሃንን ካለርህራሄ የገደለ ስብስብ በመሆኑ ከፍተኛ ቁጭት ይዘን ወደ ግዳጅ በመግባት የጠላትን ሁለት ሻምበል ሙሉ በሙሉ ደምስሰናል ብለዋል።

የጠላት ሻምበል አዛዦች ጃል ቦንሳ፣ ጃል ፈይሳ፣ ጃል መኪን የተባሉ አመራሮቹ መመታታቸውንም አረጋግጠዋል፡፡

በተጨማሪም 34 ክላሽ፣ 13 ኤስ ኬ ኤስ ኋላቀር መሳሪያ፣ ስምንት የተለያዩ ቦምቦች፣ 1 ሺህ 681 የክላሽ ጥይት፣ ትጥቆች እና የተለያዩ ወታደራዊ ቁሳቁሶች መማረካቸውን የመከላከያ ሠራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.