Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል ለመንገድ ስራ ህብረተሰቡ ከ411 ሚሊየን ብር በላይ የገንዘብ ተሳትፎ እንዳደረገ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል በመንገድ ስራ ዘርፍ ህብረተሰቡ ከ411 ሚሊየን ብር በላይ የገንዘብ መዋጮ ተሳትፎ እንደነበረው የክልሉ መንገድ ቢሮ ገለጸ፡፡

የክልሉ መንገድ ቢሮ የሰባት ወራት የስራ አፈፃፀምን በጎንደር ከተማ እየተገመገመ ነው።

የቢሮ ሀላፊው ጋሻው አወቀ (ዶ/ር)÷ በክልሉ በ2016 በጀት ዓመት 579 ፕሮጀክቶችን ለመስራት ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን ገልጸዋል።

ቢሮው 518 የመንገድ ስራ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው÷ በክልሉ የተጀመሩ የመንገድ ስራዎችን በዚህ ዓመት ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀሪ ወራት የቀሩ ስራዎችን በጥብቅ ክትትል ማጠናቀቅ ይገባል ብለዋል፡፡

የመንገድ ስራዎች በጥራትና በተሻለ ፍጥነት እንዲጠናቀቁ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ ነው ያሉት ሃላፊው÷ አንፃራዊ ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች የመንገድ ስራዎችን ለማጠናቀቅ ይሰራል ነው ያሉት፡፡

ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ሰብዓዊ ድጋፍን ለማሳለጥ ባለፉት ወራት ቢሮው የተጎዱ መንገዶችን ባደረገው ጥረት 113 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር መንገድ ጠግኗል ብለዋል፡፡

በክልሉ በተሰሩ የመንገድ ስራዎች የህብረተሰቡ ተሳትፎ ከ411 ሚሊየን ብር በላይ የገንዘብ መዋጮ ተሳትፎ እንደነበረውም ተናግረዋል።

በመንገድ ስራ ዘርፍ ለ2 ሺህ 504 ወጣቶች የስራ ዕድል መፍጠር ተችሏል።

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳደር አቶ አላምረው አበራ በበኩላቸው ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን የመንገድ ይሰራልኝ ጥያቄ ለመመለስ መንግስት ከፍተኛ ሀብት መድቦ እየሰራ ነው ብለዋል።

የተጀመሩ የመንገድ ስራዎችን ለማጠናቀቅ ህብረተሰቡ ተሳትፎውን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ጠቁመዋል።

በምናለ አየነው

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.