Fana: At a Speed of Life!

ኤጀንሲው በለይቶ ማቆያ ለሚገኙ ሰዎች 6 ሺህ መጽሐፍት ለገሰ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 28 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና መጽሐፍት ኤጀንሲ በለይቶ ማቆያ ለሚገኙ ሰዎች የሚሆኑ 6 ሺህ መጽሐፍትን ለጤና ሚኒስቴር ዛሬ ለገሰ።

መጽሐፍቱ በተለያዩ ዘውጎች የተጻፉ ሲሆኑ፥ ወደ ለይቶ ማቆያ የሚገቡ ሰዎች በቆይታቸው ወቅት ራሳቸውን በንባብ ለማበልጸግ እንደሚያስችሏቸው ተገልጿል።

መጽሐፍቱን የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ይኩኖአምላክ መዝገቡ ለጤና ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ሳህረላ አብዱላሂ አስረክበዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ በዚህ ወቅት ዜጎች ይህን አስቸጋሪ ወቅት በንባብ እንዲያሳልፉ ኤጄንሲው የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፥ የዛሬው ልገሳ አንደኛው መሆኑን አንስተዋል።

ወደ ለይቶ ማቆያ የሚገቡ ሰዎች ሃሳባቸው በተለያዩ ጉዳዮች እንዳይወሰድና ለጭንቀት እንዳይዳረጉ መጽሐፍቱ ሚና እንዳላቸው የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፥ በአዲስ አበባ ለሚገኙ ለይቶ ማቆያዎች እንደሚያገለግሉም ገልጸዋል።

በቀጣይ ለክልሎች ተመሳሳይ ድጋፍ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩንም አውስተው፥ መጽሐፍቱ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል በግለሰብ ደረጃ የሚሰጡ እንጂ በውሰት እንደማይሰጡም አስረድተዋል።

ግለሰቦቹ በለይቶ ማቆያዎች የነበራቸውን ቆይታ ሲያጠናቅቁ ወደየቤታቸው ይዘዋቸው እንደሚሄዱ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ወይዘሮ ሳህረላ በበኩላቸው በቅርቡ ወደ ለይቶ ማቆያ የገባች አንዲት ኢትዮጵያዊት በተፈጠረባት ጭንቀት ምክንያት ሕይወቷን ማጥፋቷን አስታውሰው፥ መጽሐፍቱ መሰል ችግሮችን በመፍታት ረገድ ሚናቸው የጎላ ነው ብለዋል።

ለይቶ ማቆያዎች የንባብ ባህል እንዲዳብር እገዛ እንደሚያደርጉ ጠቁመው ኤጀንሲው ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.