ዶ/ር መቅደስ ዳባ ከቢል ኤንድ ሚሊንዳ ጌትስ ፋውዴሽን ልዑካን ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ከቢል ኤንድ ሚሊንዳ ጌትስ ፋውዴሽን ልዑካን ቡድን ጋር ተወያይተዋል፡፡
የጤና ሚኒስትሯ በዚሁ ወቅት÷ በተቋማቱ መካከል ያለው ትብብር ለዘርፉ ትልቅ እድል እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ሴቶችን በማብቃት ሂደት በጋራ ለመስራት ፍላጎት እንዳለ በመግለጽ፤ በተለይ በጤና ላይ በክትባት ተደራሽነት ማስፋት፣ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መከላከል፣ በመረጃ ጂጅታላይዜሽን፣ በግጭት የተገዱ ተቋማትን መልሶ ማቋቋም፣ የእናቶች ሞት ቅነሳ፣ በፍትሀዊነት የሚታዩ አፋጣኝ ችግሮች ላይ በጋራ መስራት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡
የጤና ፋይናንስ አቅምን ለማሳደግ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ማጠናከር ላይ፣ የጤና ተቋማት የነፃ አገልግሎት ውዝፍ እዳ የሚቀልበት አሠራር ላይ ድጋፍ እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡
የቢል ኤንድ ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን የኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቶ አዲስ ደስታ ታደሰ÷ ተቋማቸው በአፍሪካ ሁለተኛው ጽህፈት ቤቱን የከፈተው በኢትዮጵያ መሆኑን አስታሰዋል፡፡
ፋውንዴሽኑ በግብርና እና ጤና ዘርፍ ላይ እየሰራ እንደሚኝ መግለጻቸውን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
ፋውንዴሽኑ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በቀጣይም በአጋርነት እንደሚሰራ ተመላክቷል፡፡
በሌላ በኩል በኢትዮጵያ የኢራን አምባሳደር መሀመድ ጃቫድ ጋር ባደረጉት ውይይት፤ ኢራን በመድሐኒትና የህክምና መሳሪያዎች ላይ ያላትን ልምድ ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት፣ የአገልግሎት አሰጣጥና ስልጠና ለማግኝት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት እንዲሁም ምርምሮች ላይ ልምድ ለመውሰድ አስቻይ ሁኔታዎች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡
በቀጣይ በሀገራቱ መካከል በጤናው ዘርፍ በጋራ የሚሰሩባቸው ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ እንደሚሰሩ ተገልጿል፡፡
አምባሳደር መሀመድ ጃቫድ በበኩላቸው÷ በኢራን እና ጤና ሚኒስቴር መካከል ሊደረጉ የታሰቡ የሁለትዮሽ ስምምነት ማዕቀፎች እንዲፈረሙ ጠይቀዋል፡፡
ስምምነትቱ በሀገራቱ መካከል ያለውን ወዳጅነት ወደ ላቀ ደረጃ ከማሳደጉም በላይ ለጤናው ዘርፍ የጋራ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡
በቀጣይ ኢራን ውስጥ በሚካሄደው ጉባኤ ላይ ሚኒስትሯ እንዲሳተፉ ግብዣ አቅርበዋል፡፡
በተጨማሪም የጤና ሚኒስትሯ÷ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ሆሴ ማሲንጋ እና ልዑካን ቡድን ጋር በኢትዮጵያና አሜሪካ መካከል በጤና ጉዳዮች ዙሪያ በትብብር ለመስራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል።
ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን በመከላከልና መቆጣጠር፣ በሰው ሃብት ልማት፣ የሕክምና አገልግሎትን በማዘመን እና በሌሎች ዘርፎች የአሜሪካ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
አምባሳደር ኧርቪን ሆሴ ማሲንጋ በበኩላቸው÷ በሰው ሃብት ልማት፣ በወባ በሽታ መከላከል፣ በስነ-ልቦና ህክምና እንዲሁም በኤችአይቪ እና በሌሎች የጤና ጉዳዮች ላይ የአሜሪካ መንግስት በትብብር ለመስራት ፍላጎት እንዳለውና ድጋፉም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።