Fana: At a Speed of Life!

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት የሀገሪቱ ታላቁ የኒሻን ሽልማት ተበረከተላቸው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ ጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከደቡብ ሱዳን ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንትና የጦር ሃይሎች ዋና አዛዥ ሳልቫ ኪር ማያርዲት የሀገሪቱ ታላቁ የኒሻን ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

ሽልማቱ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ለደቡብ ሱዳን ህዝብ ነፃነትና ሉአላዊነት መከበር ለከፈለው ታላቅ መስዋዕትነትና ላደረገው ድጋፍ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር በወቅቱ÷ ኢትዮጵያ በቸገረን ጊዜ ሁሉ መጠጊያችን እና መጠለያችን ከመሆኗም በላይ ለሀገራዊ ነፃነታችን በሺህዎች የሚቆጠሩ ልጆቿን ህይወት ጭምር በመክፈል እንደሀገር እንድንቆም አድርጋናለች ብለዋል፡፡

ዛሬም ድረስ ኢትዮጵያውያን የሠራዊታችንን አቅም በመገንባት የውስጥ ችግር ሲያጋጥመን ፈጥነው ይደርሱልናል ያሉት ፕሬዚዳንቱ÷ በዚህም ኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን ባለውለታ መሆኗን ገልፀዋል፡፡

የኒሻን ሽልማቱ ኢትዮጵያውያን ዛሬም ከጎናችን ያልተለዩና የቁርጥ ቀን ወንድሞቻችን ከመሆናቸውም በላይ በደም የተሳሰርን ማንም ሊፈታው የማይችል የአንድ ቤተሰብ ልጆች መሆናችንን የሚያረጋግጥ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በስነ- ስርዓቱ ላይ የሀገሪቱ የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም፣ የሀገሪቱ የደህንነት ከፍተኛ ሃላፊዎች፣ ጄኔራል መኮንኖችና የኢፌዴሪ መከላከያ ጄኔራል መኮንኖች መገኘታቸውን ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.