Fana: At a Speed of Life!

በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ በአንዲት ደንበኛ ላይ እንግልትና መጉላላት በፈጠሩ አመራርና ባለሙያ ላይ እርምጃ ተወሰደ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአገልግሎት አሰጣጥ ወቅት ከደንበኞች የሚሰጡ አስተያየቶችንና ሚዛናዊ ትችቶችን ተቀብሎ ፈጣን ምላሽ ለመስጠትና ለማስተካከል ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ መሆኑን የጉምሩክ ኮሚሽን ገለጸ፡፡

የጉምሩክ ኮሚሽንን ከነበረበት ውስብስብ ችግር ለማውጣት እና የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል በተደረገው እንቅስቃሴ በርካታ ፈተናዎች ማጋጠማቸውን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ አንስተዋል፡፡

በተለይም ከሕገ-ወጦች ጋር በሚደረገው ትንቅንቅ የኮሚሽኑ አመራሮች እና ሰራተኞች ህይወት እንደሚያልፍ እና የአካል ጉዳት እንደሚደርስባቸው ነው የተናገሩት፡፡

“ይህን በርካታ መስዋዕትነት ተከፍሎበት የመጣውን የተቋም ሪፎርም ጥላሸት ለመቀባት የሚጥሩ የውስጥም ሆነ የውጭ አካላትን አንታገስም ” ብለዋል፡፡

በተለይም በአገልግሎት አሰጣጥ ወቅት እንከን በሚፈጥሩ አመራሮች እና ሰራተኞች ላይ ጠንካራ እርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡

በቅርቡም በኢትዮጵያ አየር መንገድ በአንዲት ደንበኛ ላይ በደረሰው እንግልት ማዘናቸውን የገለጹት ኮሚሽነሩ÷ ችግሩን በፈጠሩ አንድ አመራር እና ባለሙያ ላይ በወቅቱ አስተዳደራዊ እና ህጋዊ እርምጃ የተወሰደ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በወቅቱ ደንበኛዋ የፈጸመችው የህግ ጥሰት እንደሌለ ጠቅሰው፤ ደንበኛዋ ለደረሰባት እንግልት እና መጉላላት በኮሚሽኑ ስም ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡

ደንበኞች እንደዚህ ዓይነት ችግር ሲያጋጥማቸው በአቅራቢያው ለሚገኙ የህግ አካላት እና በየደረጃው ለሚገኙ የኮሚሽኑ አመራሮች ማቅረብ እንደሚችሉ መናገራቸውን የኮሚሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡

በግለሰብ ደረጃ ጥፋት የሚፈጽም አመራር እና ሰራተኛ በየትኛውም ተቋም እና ጊዜ እንደሚኖር ጠቁመው÷ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታትም የተቋማትን ቅንጅታዊ ስራ ማጎልበት እና የክትትልና ቁጥጥር ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.