Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በቀጠናው ዘላቂ  ሰላምና ልማት  ለመፍጠር የምታደርገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና የጋራ ልማት፣ ዘላቂ ሰላምና የንግድ ትስስር ለመፍጠር የምታደርገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱዓለም ገለጹ።

“ቀጣናዊ ሰላም እና አብሮነት ለዘላቂ የኢኮኖሚ ትስስር” በሚል መሪ ሀሳብ የፓናል ውይይት  እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ  የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዱአለም÷በኢትዮጵያ ልማትን ለማፋጠንና የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

ከጋራ ልማት ባሻገር የውስጥ ሰላምን ለማረጋገጥ፣ ለመጠበቅና ዘላቂ ለማድረግ የሁላችንም ጥረት ያስፈልጋል ያሉት ሚኒስትሩ÷ አለመግባባትና ግጭቶች በነበሩባቸው አካባቢዎች አሁን ላይ ሰላምና መረጋጋት መፈጠሩን አስረድተዋል፡፡

የተገኘውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ በመንግስት ዘርፈ ብዙ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ጠቅሰው በአካባቢው ዘላቂ ሰላምን የሁሉም ባለድርሻ አካላት እገዛ እንዲታከልበትም ጠይቀዋል።

በመንግስት በኩል ማናቸውንም ችግሮች በውይይት የመፍታት የጸና አቋም መኖሩን  ገልፀው ለሀገር ጠቃሚውና ማንንም አትራፊ ማድረግ የሚችለው የሰላምና የውይይት አማራጭ ብቻ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

ለአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት ኢትዮጵያ የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች መሆኑንም የገለፁ ሲሆን÷ኢትዮጵያ በቀጠናው ዘላቂ ሰላም፣ልማትና የንግድ ትስስር ለመፍጠር የምታደርገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ በብዙ ችግሮች የሚፈተን መሆኑን ገልፀው  የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ በመስራት ቀጣናዊ ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚገባ መጠቆማቸውን  ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.