Fana: At a Speed of Life!

ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ አሜሪካ የቻይናን ዕድገት በበጎ ማየት እንዳለባት አስገነዘቡ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በራሷ የምትተማመን፣ ግልፅ እና የበለፀገች አሜሪካን በማየቷ ቻይና ደስ እንደሚላት ሁሉ አሜሪካም የቻይናን ዕድገት በአዎንታዊ መልኩ ማየት እንደሚጠበቅባት ፕሬዚዳንት ሺ አስገነዘቡ፡፡

ፕሬዚዳንቱ ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ጋር በቤጂንግ በሁለትዮሽ፣ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም “የቻይና እና የአሜሪካ ግንኙነት ወደፊት እንዲራመድ በትክክል መቆለፍ እንዳለበት የሸሚዝ ቁልፍ ሁሉ መሰረታዊ ትኩረት ይፈልጋል” ብለዋል ፕሬዚዳንቱ፡፡

45 ዓመት የሞላው የሀገራቱ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትም በውጣ ውረዶች ቢያልፍም ጠቃሚ ክንውኖች እንደነበሩትም አስታውሰዋል፡፡

ቻይና እና አሜሪካ ከተፎካካሪነት አጋርነትን፣ ከመጎዳዳት መረዳዳትን፣ የጋራ አቋም በመፈለግም ከፉክክር ይልቅ ልዩነቶችን ማክበር እና በተግባር ቃልን ማክበር እንዳለባቸው በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

መሬት የቻይና እና አሜሪካን የጋራ ልማት እና ብልጽግናን ማስተናገድ የምትችል ትልቅ ፕላኔት ናት ያሉት ሺ÷ በቻይና ዕድገት አሜሪካ ልትደሰት ይገባል ማለታቸውን ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡

አንቶኒ ብሊንከን በበኩላቸው ከፕሬዚዳንቱ ጋር በቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች እንዲሁም የሁለቱ ሀገሮች የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ላይ ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸውን በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡

በሀገራቱ መካከል ትብብርን ለማጠናከር በሚደረጉ ጥረቶችም አሜሪካ ጥቅሟን እና ዕሴቷን መጠበቋ እንደሚቀጥል አመላክተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.