Fana: At a Speed of Life!

በኮሪደር ልማት የተነሳው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ሕንጻ የመልሶ ግንባታ ሥራ ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኮሪደር ልማት ምክንያት ተነስቶ የነበረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ሕንጻ በአዲስ መልክ የመልሶ ግንባታ ሥራ መጀመሩን ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታወቁ፡፡

በግንባታው ማስጀመሪያም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የቤተ-ክርስቲያኗ እና የከተማ አሥተዳደሩ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን የከተማ ፕላን እና ልማት እንዲጠበቅ ብሎም ከተማችን እንድትለማ፣ እንድትዘምን እና የተሻለ ዲዛይን እንዲተገበር በርካታ ትብብር አድርጋለች ሲሉም ከንቲባዋ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል፡፡

ለዚህም በዛሬው ዕለት የመልሶ ግንባታ ሥራው የተጀመረው ሕንጻ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል።

አዲሱ ሕንጻም ከመሬት በታች ለመኪና ማቆሚያ የሚያገለግል ወለል እንደሚኖረው እና በአጠቃላይ ባለ አራት ወለል ሕንጻ ሆኖ እንደሚገነባም ጠቁመዋል፡፡

ይህም ከአካባቢው ልማት፣ ፕላን፣ በዙሪያው ካሉ ሌሎች ቅርሶች እንዲሁም ከዓድዋ ድል መታሰቢያ ጋር የሚናበብ ይሆናል ነው ያሉት፡፡

ግንባታውን በአጭር ጊዜ ውስጥ አጠናቅቀን ለቤተክርስቲያኗ የምናስረክብ ይሆናል ያሉት ከንቲባዋ÷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን አባቶች የልማት ኮሪደር ሥራውን በመደገፍ ከጎናችን ስለቆሙም እናመሰግናለን ብለዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.