Fana: At a Speed of Life!

እነ አቶ ምትኩ ካሳ በተከሰሱበት ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ እንዲከላከሉ ብይን ተሰጠ

 

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የቀድሞ የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር የነበሩት እነ አቶ ምትኩ ካሳ በተከሰሱበት ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ እንዲከላከሉ ብይን ተሰጠ።

የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 5ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በተከሳሾቹ ላይ ዐቃቤ ሕግ ያቀረበውን የሰው ምስክር ቃልና የሰነድ ማስረጃን መርምሮ ብይን ሰጥቷል።

የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በየደረጃው ተሳትፏቸው ተጠቅሶ የተረጂዎችን ቁጥር በማጋነን የተለያዩ የእርዳታ ዓይነቶችን ከመጋዘን ወጪ በማድረግ ለተረጂዎች ሳይደርስ ተሽጦ ለግል ጥቅም ውሏል በማለት የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 (1) ሀ እንዲሁም 33 እና የሙስና ወንጀልን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁ.881/2007 አንቀጽ 9 ንዑስ ቁጥር 3 እና በህገወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብን ወይም ንብረትን ምንጩን ደብቆ ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል ክስ በነሃሴ ወር 2014 ዓ.ም መመስረቱ ይታወሳል።

ክሱ ቀርቦባቸው የነበሩት 1ኛ ተከሳሽ የቀድሞ የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር የነበሩት አቶ ምትኩ ካሳ፣
2ኛ ተከሳሽ የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የፋይናንስ ዳይሬክተር አቶ አርጋው ለማ፣
3ኛ የኤልሻዳይ ሪሊፍ ኤንድ ዴቭሎፕመንት አሶሴሸን ዋና ዳይሬክተር የማነ ወ/ማሪያም፣
4ኛ ተከሳሽ ያልተያዘ ዶ/ር ዮናስ ወ/ትንሳኤ፣
5ኛ በኤልሻዳይ ድርጅት የፋይናንስ ዘርፍ ም/ስራ አስኪያጅ አቶ ደሞዝ ሀይሉ፣
6ኛ የአቶ ምትኩ ባለቤት ወ/ሮ ሶፊያ ጀማል፣
7ኛ ተከሳሽ የአቶ ምትኩ ልጅ ወ/ሮ ሚልካ ምትኩ፣
8ኛ ተከሳሽ የአቶ ምትኩ ልጅ እያሱ ምትኩ፣
9ኛ ተከሳሽ ያልተያዘ የኤልሻዳይ ድርጅት የመጋዘን ንብረት መዝጋቢ አቶ መብራቱ አሰፋ ወ/ማርያም፣
10ኛ የኤልሻዳይ ድርጅት ስቶር ኦፊሰርና የመጋዘን ንብረት ክፍል ሰራተኛ አቶ ገ/ሚኤል አብርሐ እና በግል ስራ የሚተዳደሩት
11ኛ ተከሳሽ አቶ ዮሀንስ በላይ፣
12ኛ ተከሳሽ ጌቱ አስራት እንዲሁም
13ኛ ተከሳሽ ወ/ሮ ህይወት ከበደ ነበሩ።

ከተከሳሾቹ መካከል ከ2ኛ እስከ 5ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች እና በ9ኛ፣ 10ኛ እና 12ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች ባለመያዛቸውና ችሎት ባለመቅረባቸው ምክንያት እስኪያዙ ለጊዜው ክሳቸው እንዲቋረጥ ተደርጎል።

ቀሪ ተከሳሾች 1ኛ፣ 6ኛ፣ 7ኛ፣ 8ኛ፣ 11ኛ እና 13ኛ ተከሳሾች ግን ችሎት እየቀረቡ ጉዳያቸውን ሲከታተሉ ቆይተዋል።

በክሱ ዝርዝር ላይ የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር የነበሩት አቶ ምትኩ ካሳ ኤልሻዳይ ሪሊፍ ኤንድ ዴቭሎፕመንት አሶሴሸን ዳይሬክተር የማነ ወ/ማሪያም እና ከሌሎችም ሰራተኞች ጋር ያልተገባ የጥቅም ግንኙነት በመፍጠር በሺዎች በሚቆጠሩ ተረጂዎች ስም እንዲሁም የተረጂዎችን ቁጥር በማጋነን ለበርካታ ጊዜያት እህልና የምግብ ቁሳቁሶች ከኮሚሽኑ መጋዘን በማውጣት ለተረጂዎች ሳይደርስ ለዱቄት ፋብሪካዎችና ለሌሎች ግለሰቦች በመሸጥ ህገወጥ ጥቅም ሲያገኙ እንደነበር እና ለዚህም ስራ አቶ ምትኩ ካሳ በቤተሰቦቻቸው ስም ከሌልሻዳይ ድርጅት በተለያዩ ጊዜያት ተፈጽሟል ከተባለ የሙስና ወንጀል ጋር ተያይዞ ቀርቧል።

በዚህም በአማራ፣ አፋር፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ የግብረሰናይ ድርጅቱ ማዕከላት የተረጂዎችን ቁጥር በማጋነን ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ እህልና ቁሳቁሶችን ከኮሚሽኑ በመውሰድ ለተረጂዎች ሳያደርሱ በመሸጥ ለግል ጥቅም ማዋል፣ ብድርና ድጋፍ በሚል ሰበብ በህገወጥ መንገድ ከኮሚሽኑ በመቶ ሚሊየን የሚገመት ለእርዳታ ድርጅቱ በገንዘብ መልክ መሰጠቱ በክሱ ተመላክቷል።

በተለይም 601 ሺህ 668 ኩንታል ስንዴ፣ 41 ሺህ 789 ኩንታል በቆሎ፣ ከ78 ሺህ 386 ሊትር ዘይት፣ 3 ሺህ 999 ኩንታል ሩዝ በላይ ከተራድኦ ድርጅቱና የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ጋር በመመሳጠር እርዳታውን አዳማ በሚገኝ የዱቄት ፋብሪካ መሸጡ ተጠቅሷል።

በሁለተኛ ክስ ደግሞ 472 ሚሊየን 886 ሺህ 304 ብር ከ32 ሳንቲም በድጋፍ መልክ በ1ኛ ተከሳሽ ፈቃጅነት በ2ኛ ተከሳሽ አማካኝነት ክፍያ እንደተፈጸመና በ3ኛ ተከሳሽ ወጪ አድራጊነት ለግል ጥቅም በመዋሉ በመንግስት ከፍተኛ ኪሳራ የደረሰ መሆኑ ተጠቅሷል።

የአቶ ምትኩ ልጆች እና ባለቤታቸውን በተመለከተ ደግሞ በስማቸው ተገዝተው የተገኙ ተሽከርካሪዎች እና መኖሪያ ቤቶች መኖራቸው በክሱ የተጠቀሰ ሲሆን በህገወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብን ወይም ንብረትን ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ በሌሎችም ተከሳሾች ላይ በየደረጃው የወንጀል ተሳትፏቸው በክሱ ተዘርዝሮ ተካቷል።

ክሱ ከደረሳቸው በኋላ በክሱ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው የዕምነት ክህደት ቃላቸውን መስጠታቸውን ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ የሰው ምስክርና የሰነድ ማስረጃ አቅርቧል።

ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን መርምሮ የቀድሞ የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር የነበሩት እነ አቶ ምትኩ ካሳ የተከሰሱበት 1ኛ እና 2ኛ ክስ ተጠቃሎ በባድ የሙስና ወንጀል እንዲከላከሉ ብይን የተሰጠ ሲሆን በተጨማሪነት አቶ ምትኩ በቀረበባቸው 3ኛ ክስ እንዲከላከሉ ብይን ተሰጥቷል።

በሌላ በኩል ፍርድ ቤቱ የአቶ ምትኩ ባለቤት ወ/ሮ ሶፊያ ጀማልና ሴት ልጃቸው ሚልካ ምትኩን በሚመለከት በቀረበባቸው በህገወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብን ወይም ንብረትን ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል።

ችሎቱ የአቶ ምትኩ ልጅ የሆነው እያሱ ምትኩ፣ 11ኛ ተከሳሽ ዮሃንስ በላይና 13ኛ ተከሳሽ ወ/ሮ ህይወት ከበደን በሚመለከት ተፈጽሟል የተባለ የወንጀል ድርጊትን በሚመለከት በዝርዝር በቂ ማስረጃ አለመሰማቱን ፍርድ ቤቱ ገልጾ ነጻ ብሏቸዋል።

እንዲከላከሉ የተባሉ ተከሳሾች የመከላከያ ማስረጃ ካላቸው ለመጠባበቅ ከግንቦት 17 እስከ 21 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.