Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዐቢይ በወሊሶ ከተማ የኦሮሚያ ክልል የዜግነት አገልግሎትን በይፋ አስጀመሩ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 6 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በወሊሶ ከተማ ተገኝተው የኦሮሚያ ክልል የዜግነት አገልግሎትን በይፋ አስጀመሩ።

በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳደር አቶ ተመስገን ጥሩነህ እና የሶማሌ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሀመድን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

በዘንድሮው የኦሮሚያ ክልል የዜግነት አገልግሎት መርሃ ግብር በክልሉ በሚገኙ 10 ሺህ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ተጨማሪ ሶስት የመማሪያ ክፍሎችን በበጎ ፈቃደኞች የማስገንባት እቅድ ተይዟል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩም በወሊሶ ሊበን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ሶስት ተጨማሪ ክፍሎችን ግንባታ አስጀምረዋል።

በተጨማሪም ለትምህርት ቤቱ ቤተ መፅሃፍት 50 ኮምፒውተሮችን እና የተለያዩ የትምህርት መርጃ መፅሃፍትን አበርክተዋል።

የመርሃ ግብሩ አካል የሆነውን በትምህርት ቤቱ ችግኝ የመትከል እና በከተማዋ የሚኖሩ አቅመ ደካማዎችን መኖሪያ ቤት የማደስ ስራንም በመሳተፍ አስጀምረዋል።

አገልግሎቱ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ መልክ አለው ተብሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህዝቡ የሚናፈሰውን አሉባልታ በመተው ለሃገር ልማትና ለውጥ እንዲተጋ እና ወጣቱም የነገ ኢንቨስትመንት በሆነው በዚህ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።

በንጹህ ልብ የሚሰራ ሰው ማንኛውንም ፈተና ያልፋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ፥ ከፊቱም ብሩህ ተስፋ ይጠብቀዋል ነው ያሉት።

እርስ በርስ ከመጠፋፋት በመታቀብም አንድ ላይ በመሆን ሃገራችንን እና ህዝባችንን እናገልግል ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።

በዚህ የዜግነት አገልግሎት አቅመ ደካሞችን እና ድሃ የህብረተሰብ ክፍሎችን ማገልገል እንደሚገባም በማንሳትም ልዩነትን ወደ ጎን በመተው ክልሉን የሚጠቅም ስራ እንስራም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው።

የኦሮሚያ ክልል በተፈጥሮ ሃብት የበለጸገ መሆኑን ጠቅሰው፥ በአንድነትና በጋራ በመስራት ወደ ብልጽግና ጎዳና እንሻገርም ነው ያሉት።

የኦሮሚያ ክልላ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው፥ ህብረተሰቡን በማሳተፍ ወደቀደመው ባህላችን ተመልሰን ተወዳዳሪ በመሆን ኦሮሚያን እንገነባለን ብለዋል።

የዜግነት አገልግሎቱ “በዜግነት አገልግሎት ኦሮሚያን እንገነባለን” በሚል መሪ ቃል ነው የሚካሄደው።

በክልሉ ከሚገነቡ 30 ሺህ ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች በተጨማሪ 560 ቤተ-መፅሀፍትን የመገንባት እና 3 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኝ የመትከል እቅድ ተይዟል።

በትዝታ ደሳለኝ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.