Fana: At a Speed of Life!

የሶማሌ ክልል በአምራች ኢንዱስትሪ የተሰማሩ ባለሀብቶችን ለመደገፍ እየሰራሁ ነው አለ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሶማሌ ክልል አምራች ኢንዱስትሪ ዘርፎች የተሰማሩ ባለሀብቶችን ለመደገፍ እየተሰራ መሆኑን የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢብራሂም ዑስማን ገለጹ ።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢብራሂም ኡስማን የተመራ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ቡድን በሲቲ ዞን ሽንሌ ወረዳ የሚገኙ የተለያዩ አምራች ፋብሪካዎችን እና የልማት ፕሮጀክቶችን ጎብኝቷል፡፡

በጉብኝታቸውም በሽንሌ ወረዳ የሚገኝ የዉሀ ፋብሪካ ፣ ዘመናዊ የዶሮ እርባታ እና የእምነበረድ ፋብሪካን የስራ እንቅስቃሴ መመልከታቸው ተገልጿል ፡፡

1ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ወጪ የተደረገበት የእምነበርድ ፋብሪካው ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል መፍጠሩ ተጠቁሟል፡፡

አቶ ኢብራሂም ኡስማን በዚሁ ጊዜ እንዳሉት÷ የክልሉ መንግስት በተለያዩ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፎች የተሰማሩ ባለሀብችን ለመደገፍና የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ ለመስጠት በትኩረት እየሰራ ነው፡፡

አመራሮቹ ከዚህ በተጨማሪም በሽንሌ ወረዳ እየተገነቡ ያሉ የሪልእስቴት ግንባታዎችን የጎበኙ ሲሆን÷ የሪል እስቴት ግንባታው በመጠናቀቅ ላይ እንደሆነ እና በአጠቃላይ ለመገንባት ከታቀደው 600 ቤቶች እስካሁን 250 ቤቶች ግንባታ መጠናቀቁ ተገልጿል፡፡

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር በሽንሌ ወረዳ ቆይታቸው የመርማርሳ አዳሪ ትምህርት ቤትን እና በትምህርት ቤቱ ግቢ ውስጥ እየለሙ የሚገኙ አትክልትና ፍራፍሬዎችን እና አጠቃላይ የትምህርት ቤቱን የስራ ሂደትም መመለከታቸውን ከክልሉ የመገናኛ ብዙሃን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በተመሳሳይ አቶ ኢብራሂምና የክልሉ አመራሮች በድሬዳዋ የሚገኘውን የብሔራዊ ሲሚንቶ ፋብሪካ የጎበኙ ሲሆን÷ ከጉብኝቱ በኋላም ከፋሪካው የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመምከር የሚፈለገውን የሲሚንቶ ፍላጎት ለሟሟላት እንዲቻል በትኩረት እንዲሠራ አሳስበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.