ቬልቬክስ ፣ ዞይ የተባሉ የእጅ ማፅጃ ኬሚካል( ሳኒታየዘሮች) እና የፓዮኔር ቀይ ወይን ጭማቂ ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ተከለከለ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ቬልቬክስ እና ዞይ የተባሉ የእጅ ማፅጃ ኬሚካል( ሳኒታየዘሮች) እና የፓዮኔር ቀይ ወይን ጭማቂዎ ጥቅም ላይ እንዳይውሉ መከልከሉን የኢፌዴሪ የንግድ ውድድር እና ሸማቶች ጥበቃ ባልስልጣን አስታወቀ።
ሁለቱ ምርቶች በውስጣቸው ያለው አልኮል መጠን ከደረጃ በታች በመሆኑ ጥቅም ላይ እንዳይውሉ መታገዱን ባለስልጣኑ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ ላይ ገልጿል።
መቀመጫቸውን ኬኒያ ባደረጉ አምራቾች የሚመረቱት ሁለቱ የሳኒታይዘር አይነቶች፤ ተጠቃሚዎችን ከበሽታ አምጪ ተህዋስያን የመጠበቅ ሃይል እንደሌላቸው መረጋገጡንም ባለስልጣኑ አሳውቋል።
በተመሳሳይ ባለስልጣኑ የፓዮኔር ምግብ አምራች ምርት የሆኑ የተወሰኑ የቀይ ወይን ጭማቂ ምርቶች ላይ የጠርሙስ ስብርባሪ በመገኘቱ ምርቶቹ ከገበያ እንዲሰበሰቡ አዟል።
ባለስልጣኑ እንደገለፀው፤ ኮዳቸው በባለስልጣኑ የተገለፁ ምርቶች ለቅድመ ጥንቃቄ ሲባል ለሽያጭ እና ለፍጆታ እንዳይወሉ ታግደዋል።
ህብረተሰቡ ይህንን በመገንዘብ ቬልቬክስ እና ዙይ ሳኒታይዘሮችን እና የፓዮኔር ቀይ ወይን ጭማቂዎችን ከመጠቀም እንዲታቀብም ባለስልጣኑ አሳስቧል።