Fana: At a Speed of Life!

አትሌት ለተሰንበት ግደይ አቀባበል ተደረገላት

አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በስፔን ቫሌንሺያ የሴቶችን የ5 ሺህ ሜትር ክብረወሰን የሰበረችው አትሌት ለተሰንበት ግደይ አቀባበል ተደረገላት፡፡

ለተሰንበት ከዋና አሰልጣኟ ኃይሌ እያሱ ጋር ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ስትደርስ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ደራርቱ ቱሉ፣ አትሌት ማርቆስ ገነቴ የኢትዮጵያ አትሌቶች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ቢልልኝ መቆያ የፌዴሬሽኑ ፅህፈት ቤት ኃላፊ በስፍራው ተገኝተው አቀባባል አድርገውላታል፡፡

የ22 ዓመቷ ለተሰንበት ከትናንት በስቲያ ሌሊት የተካሄደውን የ5 ሺህ ሜትር ሩጫ ውድድር 14 ደቂቃ ከ6 ሰከንድ ከ62 ማይክሮ ሰከንድ በሆነ ጊዜ በመግባት ማሸነፏ ይታወሳል፡፡

ይህን ተከትሎም በሌላኛው ኢትዮጵያዊት አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ተይዞ የነበረውን የሴቶች የ5 ሺህ ሜትር ክብረ ወሰን አሻሽላለች፡፡

ከዚህ ቀደም ከ12 ዓመታት በፊት በ14 ደቂቃ ከ11 ሰከንድ ከ15 ማይክሮሰከንድ በሆነ ጊዜ ጥሩነሽ ዲባባ የርቀቱ ክብረ ወሰን ባለቤት እንደነበረች የሚታወስ ነው፡፡

ለተሰንበት በወቅቱ ማሸነፏን ተከትሎ በሰጠችው አስተያየት የረጅም ጊዜ ህልሟ እንደነበር ጠቅሳ በማሸነፏ መደሰቷን ገልጻለች፡፡

ፌዴሬሽኑ የለተሰንበት ድል ለአመራሮቹና ሠራተኞቹ ተጨማሪ መነሳሳትን እንደፈጠረ ገልጿል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.