አየር መንገዱ በሶስት የቻይና ከተሞች አዲስ በረራ ሊጀምር ነው
አዲስ አበባ፣ ጥር4 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሶስት የቻይና ከተሞች አዲስ በረራ ሊጀምር ነው።
አዲሱ በረራ ወደ ቾንግቂንግ፣ ሼንዠን እና ዠንግዡ ከተሞች እንደሚጀመር የአየር መንገዱ ኮሙዩኒኬሽን ባለሙያ አቶ ዳዊት ተመስገን ለሺንዋ ተናግረዋል።
አሁን ላይ አየር መንገዱ በረራውን ለመጀመር ፈቃድ መጠየቁን ያነሱት አቶ ዳዊት፥ ፈቃዱን ካገኘ በኋላ በረራውን ይጀምራል ብለዋል።
አያይዘውም አየር መንገዱ በተለይም እንደ ጉዋንዡ ባሉ ከተሞች የሚያደርገውን በረራ በቀን ወደ ሁለት ጊዜ በማድረግ በቻይና የሚሰጠውን አገልግሎት የማስፋት እቅድ እንዳለውም ተናግረዋል።
አየር መንገዱ አሁን ላይ ከአዲስ አበባ ጉዋንዡ እና ቤጂንግ በየቀኑ እንዲሁም ወደ ቼንግዱ ከተማ በሳምንት ሶስት ቀን በረራ ያደርጋል።
ምንጭ፦ ሺንዋ