Fana: At a Speed of Life!

መንግስት በምርጫ ሂደቱ ሊከሰቱ የሚችሉ የጸጥታ ችግሮችን በመለየት እርምጃ እየወሰደ መሆኑ ተገለፀ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 2 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)በምርጫ ሂደቱ ሊከሰቱ የሚችሉ የጸጥታ ችግሮችን በመለየት እርምጃ እየወሰደ መሆኑን መንግስት አስታውቋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ በተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋለው የፀጥታ ችግር በምርጫ እንቅስቃሴው ላይ እንከን መፍጠሩን ጠቅሰዋል።
በአንዳንድ አካባቢዎች ያለው የጸጥታ ችግር የምርጫ ቁሳቁሶችን ወደ ምርጫ ጣቢያዎች የማጓጓዝ፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች በነፃነት ተንቀሳቅሰው ለመስራት እንቅፋት ፈጥሮ መቆየቱን ተናግረዋል።
በመሆኑም መንግስት ከቦርዱ ጋር በመነጋገር የጸጥታ ችግሮች መፍትሔ እንዲያገኙ በጋራ እየሰሩ በመሆኑን ዶክተር ቢቂላ ገልጸዋል።
ዜጎች በምርጫው ላይ ያለፀጥታ ስጋት ተሳትፎ እንዲያደርጉ መንግስት ሰላምና ጸጥታ ማስከበር ስራውን በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በ2013 ዓ.ም ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ይካሄዳል ተብሎ ይፋ ከተደረገበት ጊዜ አንስቶ መንግስት አገራዊ እቅድ አውጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል።
በዚህ ረገድም የፖሊስና ደህንነት ተቋማትን ያቀፈ ብሔራዊ የደህንነት ግብረ ሃይል ተቋቁሞ በቅድመ ምርጫ ሂደት ሊከሰቱ የሚችሉ የጸጥታ ችግሮችን በመለየት እርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በምርጫ ዕለትና ከምርጫው በኋላ የግጭት መንስኤ ሊሆኑ የሚችሉ ሁኔታዎችን የመለየትና የመተንተን ስራዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል።
በሌላ በኩል ዓለም አቀፍ ተቋማት ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ቢታዘቡ መልካም እንደሆነ የገለጹት ዶክተር ቢቂላ የታዛቢዎቹ መቅረት በምርጫው ሂደት ላይ የሚያሳድረው ጉዳት እንደማይኖር ተናግረዋል።
ምርጫው ስኬታማ እንዲሆን የሚያደርገው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንጂ ሌላ የውጭ አካል አይደለምም ነው ያሉት።
ምርጫው ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሃላፊነት እንዲወጡም ጥሪ ማቅረቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.