Fana: At a Speed of Life!

አዲስ ወግ “ፅናት ለሀገር ህልውና” በሚል ርዕስ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 19 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) አዲስ ወግ የውይይት መድረክ “ፅናት ለሀገር ህልውና” በሚል ርዕስ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት እየተካሄደ ነው።

መድረኩ ምጣኔ ሐብት፣ ስነ ልቦና፣ ኪነ ጥበብ እና ደህንነት ላይ ትኩረቱን አድርጎ እንደሚካሄድ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

“ለውጡ መዋቅር፣ አደረጃጀት፣ የመለዮ ጥቅማ ጥቅም ደመወዝና የሕይወት ካሳ ማሻሻያዎችን አድርጎ መከላከያን ገለልተኛ ተቋም ለማድረግ ተግቷል” ያሉት የመከላከያ ሠራዊት ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ናቸው።

ሠራዊቱ ባነሰ ቁጥርና መሣሪያ ተሰልፎ የሀገርን ንብረት ማስመለስ መቻሉንም ገልጸዋል።

“ሁኔታው ሕዝባችንን ወደ አንድነት አምጥቶታል፤ የእንስት አባላትን አስደናቂ ብቃት ገልጧል፤ በርካቶች ወደ ሠራዊቱ ተቀላቅለዋል፤ ሀገራችን ባለ ጽኑ መሠረት እንጂ ማንም የሚንዳት የጨረቃ ቤት አይደለችም” ብለዋል ኮሎኔል ጌትነት ፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ አማካሪ ማሞ ምህረቱ በበኩላቸው፥ ችግሮችን ተቋቁሞ ሀገርን ማስቀጠል ማለት የነበረውን እንደ ነበር ይዞ መጓዝ ሳይሆን ችግሮችን ወደ ዕድል ቀይሮ ወደ ከፍታ መጓዝ መሆኑን አንስተዋል።

ምርት እና ምርታማነት እንዲጨምር፣ የዕዳ ቅነሳ እና ስረዛ፣ የውጪ ምንዛሬ አቅምን መጨመር እና ገቢን የማጠናከር ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውን ያነሱት አማካሪው፥ ከተወሰዱ እርምጃዎች መካከል የዋጋ ንረት ከፍተኛ ለውጥ አለማስገኘቱን ጠቅሰዋል።

ለእርሱም አፋጣኝና ልዩ ልዩ መፍትሔዎች ሊተገበሩ መሆኑን በመጥቀስ፥ ፅናት የተግዳሮት ያለመኖር ሳይሆን ተግዳሮትን ወደ ዕድል፣ ዕድልን ደግሞ ወደ ድል መለወጥ መሆኑን አስረድተዋል።

የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ ጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ሃላፊ ሰርፀ ፍሬስብሀት፥ ኪነ ጥበብ በየወቅቱ ሀገር የገጠማትን ተግዳሮት በጀግንነት እንድታልፍ አስተዋጽኦ ማበርከቷን ጠቁመዋል።

በዚህ ዘርፍ የሚጠቀሱ አንጋፋ ባለሙያዎች እንዳሉ በማውሳትም፥ ከለውጡ በፊት የደረሰው ተቋማዊ ስብራት ይህንን አቅም ክፉኛ ቢገዳደርም ኪነ ጥበብ በእጅጉ ወሳኝ ሚና እንዳለውም ገልጸዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.