Fana: At a Speed of Life!

ህብረተሰቡ ሊፈጠር ከሚችል የወንዞች ሙላትና ቅፅበታዊ የጎርፍ አደጋ ራሱን ሊጠብቅ ይገባል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 30፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ህብረተሰቡ በያዝነው ክረምት ወቅት ሊፈጠር ከሚችል የወንዞች ሙላት እና ከጎርፍ አደጋ ራሱን ሊጠብቅ እንደሚገባ የብሔራዊ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽንና ብሄራዊ ሜትሪዮሎጂ ኤጀንሲ አሳሰቡ።

ጉዳዩ የሚመለከታቸው የሁለቱ ተቋማት የስራ ሃላፊዎች ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ ነገ በሚጀምረው የነሃሴ ወርም መደበኛ እና ከመደበኛ በላይ ዝናብ መዝነቡ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ሰሜናዊ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ሱዳን እንዲሁም የእነዚህ ሀገራት አዋሳኝ አካባቢዎች በቀጣዮች ቀናት ከባድ ዝናብ እንደሚያስተናግዱም የኢጋድ የአየር ንብረት ለውጥ ቅድመ ትንበያ ቢሮ ትናንት  ይፋ አድርጓል።

በብሄራዊ ሚትዮሮሎጂ ኤጀንሲ የትንበያ እና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ዳይሬክተር ወይዘሮ ጫሊ ደበሌ፥  ነገ በሚገባው የነሃሴ ወር የዝናብ መጠን ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ አሁን እየጣለ ያለው ዝናብ ጠቀሜታ እንዳለው ያብራሩት ዳይሬክተሯ፥ በተቃራኒውም ጉዳቶችን ሊያደርስ እንደሚችልም ነው የተናገሩት።

ወይዘሮ ጫሊ፥ ህብረተሰቡ የሚጥለውን ከዳብ ዝናብ ተከትሎ በቀጣይ ሊከሰት ከሚችለው የጎርፍ አደጋ ራሱን መጠበቅ ይገባዋል ሲሉም መልእክት አስተላልፈዋል።

የብሔራዊ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን የቅድመ ማስጠንቀቂያ ቡድን መሪ አቶ ነግዬ ሃይሉ በበኩላቸው፥ በኢትዮጵያ ከባድ ዝናብ ሲጥል  ለጎርፍ ተጋላጭ  መለየታቸውን ጠቅሰዋል።

አቶ ነግዬ  አደጋ በደረሰባቸው አካባቢዎችም ኮሚሽኑ እያደረገው ያለውን ድጋፍ ያብራሩ ሲሆን፥ በወንዝ ሙላት ምክንያት በአፋር ክልል ተጎጂ የሆኑ ህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም ገልፀዋል።

የሁለቱ ተቋማት የስራ ሃላፊዎች እንደተናገሩት ህብረተሰቡ የአየር ፀባይ ትንበያዎችን በአግባቡ በመከታተል ራሱን ከአደጋ ቀጣናዎች ማራቅ ይኖርበታል ብለዋል።

በስላባት ማናዬ

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.