Fana: At a Speed of Life!

ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በጋምቤላ እና ምዕራብ ወለጋ ዞን አሸባሪው ሸኔ በንፁሃን ዜጎች ላይ የፈጸመውን አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አጣርቶ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጠ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በጋምቤላ ክልል እና በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን በአሸባሪውና ተላላኪው ሸኔ በንፁሃን ዜጎች ላይ የተፈጸመውን አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አጣርቶ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
 
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ ÷የምክር ቤቱ አባላት ከመራጭ ህዝብ ጋር በተወያዩበት ወቅት ህዝቡ መንግስት የዜጎችን ሠላም፣ ደህንነት እና የየአካባቢውን ፀጥታ እንዲያስከብር ጥያቄ በከፍተኛ ደረጃ ሲያቀርብ መቆየቱን አንስቷል፡፡
 
የህዝቡን ጥያቄ መነሻ በማድረግም መንግሥት ህግ የማስከበር ህገ-መንግሥታዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት አስፈላጊውን እያደረገ ይገኛል ነው ያለው፡፡
 
በህግ የማስከበር ዘመቻ ላይ የተለያዩ ቅሬታዎች መነሳታቸውን መነሻ በማድረግም የህግ ፍትህና ዴሞክራሲያዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች ያለአግባብ በህግ ቁጥጥር ስር የዋሉ ሰዎች አሉ በሚል የቀረበውን ቅሬታ መነሻ በማድረግ በአስቸኳይ ማጣራት አደርጎ ለምክር ቤቱ እንዲያቀርብ ተልዕኮ ተሰጥቶት ሥራ ላይ እንደሚገኝ ተመላክቷል፡፡
 
በሌላ በኩል ሰሞኑን በጋምቤላ ክልል እና በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ውስጥ በተወሰኑ አካባቢዎች በአሸባሪውና ተላላኪው ሸኔ በንፁሃን ዜጎች ላይ እጅግ አሰቃቂ፣ አሳዛኝና በሰው ልጆች ላይ መፈፀም የሌለበት ግፍ መፈጸሙን ምክር ቤቱ በመግለጫው አመላክቷል፡፡
 
ምክር ቤቱ የተፈጸመውን ግፍ ሂደት ማጣራትና ተገቢውን ድጋፍ መስጠት አስፈላጊ ነው ብሎ እንደሚያምንም አስታውቋል፡፡
 
በዚህ መሰረትም ምክር ቤቱ በሂደቱ የደረሰው ጉዳት መጠን እና የሚያስፈልገው አስቸኳይ ድጋፍ በቋሚ ኮሚቴው በኩል ተጣርቶ እንዲቀርብ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡
 
የሚቀርበውን የጉዳት መጠን መረጃ መነሻ በማድረግም የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ተከታትሎ አስፈላጊውን ድጋፍ በአስቸኳይ ለዜጎች እንዲያቀርብ መመሪያ መስጠቱን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
 
ከዚህ ባለፈም ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በሂደቱ ከሰብዓዊ መብት ጋር ተያይዞ የተፈጸሙ ጉዳዮችን አጣርቶ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡
 
መረጃ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ እና ምላሽ መስጠት ይቻል ዘንድም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አቶ ታገሠ ጫፎ ከምክር ቤት አባላት የተውጣጡ ወቅታዊ ጉዳዮችን የሚያጣሩ ሁለት ቡድኖችን በማቋቋም ስምሪት መስጠታቸው ታውቋል፡፡
 
ቡድኖቹ ሥራቸውን እንደጨረሱ ውጤቱን ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርጉ እና አስፈላጊ አቅጣጫ እንደሚሰጥበትም አፈ ጉባዔው አስታውቀዋል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.