Fana: At a Speed of Life!

16ኛው የኢትዮ-ጅቡቲ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን መድረክ ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የነበረው 16ኛው የኢትዮጵያና ጅቡቲ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን የግማሽ ዓመት አፈጻጸም መገምገሚያ መድረክ በስምምነት ተጠናቀቀ፡፡

በመድረኩ ስምምነት ላይ የተደረሰባቸውን ጉዳዮች እንዲሁም በስምምነቱ ወቅት በሁለቱም ወገን ክትትል ተደርጎባቸው መፍትሄ እንዲሰጥባቸው አቅጣጫ የተቀመጠላቸው ጉዳዮች አፈጻጸም ተገምግሟል፡፡

በሀገራቱ ሁሉን አቀፍ የትብብር ማዕቀፎች፣ በኢንቨስትመንትና በሕገ-ወጥ የጠረፍ ንግድ፣ በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ በትራንስፖርት እና ሎጅስቲክ ዘርፎች ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡

በተለይም በዲኪል – ጋላፊ መንገድ ግንባታ አፈፀፃምና የመንገድ ፈንድ ክፍያ፣ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የወደብና ትራንዚት እንዲሁም በጉምሩክ አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ያሉ ማነቆዎችን ለመፍታት እየተደረጉ ባሉት ጥረቶች ላይ የሴክተሮች ትብብርና የተገኙ ምላሾች ላይ ምክክር መደረጉም ተገልጿል፡፡

በዚህ መነሻም በሀገራቱ መካከል ከዚህ ቀደም የተፈረሙ የወደብ እና ትራንዚት አገልግሎቶች፣ የጉምሩክ ፕሮቶኮል ስምምነት እና የመልቲሞዳል ስምምነቶችን ለማሻሻል የቴክኒክ ኮሚቴዎች ተዋቅረው በመጪው ሐምሌ 2016 ዓ.ም በጅቡቲ በሚካሄደው 17ኛው የሚኒስትሮች የጋራ ምክክር መድረክ ምክክር የሚደረግባቸውን የትኩረት አቅጣጫዎች በማስቀመጥ መድረኩ በስምምነት ተጠናቋል፡፡

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ በውይይቱ የኢትዮጵያ እና የጅቡቲ ለረዥም ጊዜ የቆየ የጠበቀ ወዳጅነትን መሠረት ያደረገ ምክክር መደረጉን አንስተዋል፡፡

ውይይት የተደረገባቸውና ስምምነት የተደረሰባቸው እንዲሁም በቀጣይ ትኩረት የሚሹ ተብለው በተቀመጡ አጀንዳዎች ላይ ከሁለቱም አካላት የሚመለከታቻው ተቋማት ተገናኝተው በመወያየት አስፈላጊውን ሥራ እንደሚያከናውኑ እምነታቸውን ገልፀዋል፡፡

በተለይም ለወደብ ሎጂስቲክስ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት በቅንጅት መሠራት እንዳለበት በአጽንኦት መግለጻቸውን በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመላክታል፡፡

የጅቡቲ የመሰረተ-ልማት ሚኒስትር ሀሰን ሁማድ በበኩላቸው መድረኩ በጥሩ መንፈስ መካሄዱን ገልጸው፤ የኢትዮጵያንና የጅቡቲን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር መሰል መድረኮች ትልቅ አስተዋዕጽኦ እንዳላቸው አስገንዝበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.