Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያና ኮንጎ ሪፐብሊክ በአየር ትራንስፖርት ዘርፍ በጋራ ለመሥራት ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ እና ኮንጎ ሪፐብሊክ መካከል በአየር ትራንስፖርት ዘርፍ በጋራ ለመሥራት የሚያስችል የሁለትዮሽ ስምምነት ተፈረመ፡፡

ሁለቱ ሀገራት በአየር ትራንስፖርት ዘርፍ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት የፈረሙት የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) እና የኮንጎ ሪፐብሊክ የትራንስፖርት ሲቪል አቪዬሽን መርቻንት ኔቪ ሚኒስትር ኦነሬ ሳይ ናቸው፡፡

ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንዳሉት÷ የአየር ትራንስፖርት ለሁንተናዊ ሀገራዊ ዕድገት ከሚጫወተው ወሳኝ ሚና ባሻገር በአፍሪካም የኢኮኖሚ እና የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር በመፍጠር ረገድ ቁልፍ ሚና አለው፡፡

ይህን በመገንዘብም ኢትዮጵያ እስከአሁን በሁሉም አኅጉራት ከሚገኙ 112 ሀገራት ጋር የአየር አገልግሎት ስምምነቶችን ተፈራርማለች ማለታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡

ኢትዮጵያ እና ኮንጎ ሪፐብሊክ የረጅም ጊዜ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳላቸው አስታውሰው÷ በቀጣናዊ እና አኅጉራዊ ድርጅቶች ውስጥ በትብብር ላይ የተመሠረተ የጋራ አቋሞችን በንቃት በማራመድ የአፍሪካ ኅብረት ዓላማዎች እንዲሳኩ የድርሻቸውን እየተወጡ የሚገኙ ወዳጅ ሀገሮች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

ኦነሬ ሳይ በበኩላቸው በሀገራቱ መካከል ዛሬ የተፈረመው ስምምነት ግንኙነታቸውን ይበልጥ እንደሚያጠናክር ገልጸው÷ ስምምነቱ በቀጣይ በአቪዬሽን ዘርፍ በጋራ ለመስራት እና በዘርፉ የተቀመጡ ግቦችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።

ስምምነቱ ከዚህ ቀደም በአጭር ፊርማ ደረጃ የነበረውን ስምምነት የአፍሪካ አየር መንገዶች በአፍሪካ አየር ክልል ላይ ያለምንም ገደብ አገልግሎት ለመስጠት በሚያስችላቸው እና በአሁኑ ጊዜ በአፍሪካ ኅብረት አነሳሽነት በማሻሻል በሙሉ ፊርማ መጠናቀቁንም ገልፀዋል፡፡

ስምምነቱ በበረራ ምልልስ፣ በመዳረሻ ቦታ፣ በትራፊክ መብቶች፣ በአውሮፕላን ዓይነት፣ በተወካይ አየር መንገዶች ቁጥር እና በመሳሳሉት ጉዳዮች ላይ ገደብ ያላስቀመጠ በመሆኑ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ዲፕሎማሲያዊ ግንኝነቶችን ለማጠናከር ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ተብሏል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኮንጎ ሪፐብሊክ በሳምንት ሰባት በረራ የሚያደርግ ሲሆን÷ ይህ ስምምነት በሁለቱ ሀገራት መካከል መደረሱ ወደ ብራዛቪልና ፖይንትኖይር ከተሞች የሚያደርገውን በረራ በማጠናከር የአገልግሎት አድማሱን ለማስፋት ምቹ ሁኔታና ተጨማሪ የገበያ ዕድልን እንደሚፈጥር ተጠቅሷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.