Fana: At a Speed of Life!

በመንግስት ቀዳሚ አጀንዳነት የሰላምና ደህንነት ጉዳይ መካተቱ አስፈላጊ ነው – ምሁራን

አዲስ አበባ፣መስከረም፣25፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በመንግስት ቀዳሚ አጀንዳነት የሰላምና ደህንነት ጉዳይ መካተቱ ተጠባቂም አስፈላጊም ነው ሲሉ የህግ ምሁራን ተናገሩ፡፡

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግስት የኢትዮጵያን ህልውና ማስቀጠልን፣ ሰላምና ደህንነትን ማስጠበቅን ቀዳሚ ትኩረት በመስጠት የፀጥታ ሀይሉን የማደራጀት ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉ በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህሩ መሃመድ ሰዒድ÷ መንግስት የሀገርን ህልውና ሰላምና ደህንነት የማሥጠበቅ ሀላፊነቱን ለመወጣት፣ ቀዳሚ አጀንዳ ማድረጉ የሚጠበቅና የተገባ ነው ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ታጣቂ ቡድኖች በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸውንና ይህም በንፁሃን ላይ አደጋ መጋረጡን የገለፁት በዲላ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህሩ አቶ ሄኖክ አሻግሬ ÷አሸባሪዎቹ ህወሃትና ሸኔ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍልና በምዕራብ ኦሮሚያ የከፈቷቸውን ጥቃቶች ጨምሮ በቤኒሻንጉልና ሌሎች አካባቢዎች የነበሩ የፀጥታ ችግሮችን እንደማሳያ ተናግረዋል፡፡

ለሁሉም መሰረት የሆነው ሰላምና ደህንነት ለዜጎች መረጋጋትና ዋስትና መስጠት ቀዳሚ የመንግስት ሀላፊነት መሆኑ ተነስቷል፡፡

የህግ ምሁሩ መሀመድ ሰዒድ÷ መንግስት በተለይም በሽብር ቡድንነት የተፈረጁ ሀገርንም ለማፍረስ ለተነሱ ቡድኖች ታጋሽነቱ የማያስፈልግ ነው ይላሉ፡፡

በሌላ በኩል ምሁራኑ የኢትዮጵያ የሰላምና ደህንነት ጉዳይ ከሀገር የተሻገረ ለአፍሪካ ቀንድና ለቀይ ባህር ጂኦፖለቲካ ጠቀሜታ ያለው ስለመሆኑ አንስተዋል፡፡

ይህም የሃያላን ፍላጎት ባለበት አካባቢ የበለጠ አቅምን ማደርጀት እንደሚገባ ይጠቁማል ያሉ ሲሆን መንግስት በሚወስዳቸው እርምጃዎችም እነዚህን መሰረታዊ ጂኦ ፖለቲካዊ ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ ሊያስገባ ይገባዋል ብለዋል፡፡

በአፈወርቅ እያዩ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.