Fana: At a Speed of Life!

የታዩ መልካም ውጤቶች ይበልጥ ተጠናክረው ፣ ጉድለቶች ታርመው ስራዎቻችን ውጤታማ እንዲሆኑ ችግር ፈቺ አመራር መሆን አለብን – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

 

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሁሉም የስራ ዘርፎች የታዩ መልካም ውጤቶች ይበልጥ ተጠናክረው ፣ ጉድለቶች ታርመው ስራዎቻችን ውጤታማ እንዲሆኑ ችግር ፈቺ አመራር መሆን አለብን ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የ9 ወራት እቅድ አፈፃፀምና የቀጣይ ትኩረት አቅጣጫዎች ግምገማ አካሂዷል።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፥ ህዝቡን የፀጥታ ስራ ባለቤት በማድረግ ጠንካራ ስራ መሰራቱን አንስተው፥ በሌሎችም ዘርፎች የታዩ መልካም ውጤቶች ይበልጥ ተጠናክረው ፣ ጉድለቶች ታርመው ስራዎቻችን ውጤታማ እንዲሆኑ ችግር ፈቺ አመራር መሆን አለብን ብለዋል፡፡

ችግር መደርደር ሳይሆን ውጤት ማምጣት አለብን ያሉት ከንቲባዋ ፥ አመራሩ ራሱ ምሳሌ ሆኖ መምራት እንደሚኖርበትም ነው ያነሱት፡፡

ተቋም መገንባት፣ ተቋማዊ ቅንጅት መፍጠርና ስርዓት መገንባት አስፈላጊ ጉዳይ መሆኑን የገለጹት ከንቲባ አዳነች፥ መልካም ልምዶችን ማስፋት በሁሉም አመራሮችና በሁሉም ተቋማት እንዲተኮርበት አጽንኦት ሰጥተውበታል፡፡

ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ በበኩላቸው ፥ ከበጀት ዓመቱ ያለን ቀሪ ጊዜ አነስተኛ በመሆኑ አመራሩ በጊዜ የለኝም ስሜት በልዩ ሁኔታ ስራውን መፈፀም እንደሚገባው አሳስበዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለፉት 9 ወራት በከተማው የነበረውን አፈፃፀም ከከተማው ከፍተኛ አመራሮች ጋር በጋራ የገመገመ ሲሆን ፥ በማጠቃለያውም የቀጣይ የርብርብ ማዕከል የሆኑ አቅጣጫዎች መቀመጣቸውንም ነው ከከንቲባ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ የሚያመልከተው፡፡

በግምገማው ከሰላም አኳያ የተሰሩ መልካም እና አበረታች ስራዎች፣ ከፕሮጀክት አፈፃፀም አንፃር የታዩ ጠንካራና ደካማ ጎኖች ፣ በውሃ በመንገዶች ላይ የታዩ መልካም እንቅስቃሴዎች፣ በዲዛይንና ኮንስትራክሽን፣ በስራ እድል ፈጠራ ፣ በገቢና በትምህርት እንዲሁም በጤና ዘርፍ መልካም አፈፃፀም የታዩ ዋና ዋናዎቹ ጉዳዮች ናቸው፡፡

የኑሮ ውድነቱን ለማርገብም የተደረገው ርብርብ አበረታችን እንደነበርም የተቀመጠ ሲሆን ፥ በተቋማዊ የሪፎርም ስራዎችም በርካታ ጠንካራ እንቅስቃሴዎች መደረጋቸው ተገልጿል፡፡

በቀጣይ በከተማው ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫ ተብለው ከተቀመጡ ጉዳዮች መካክል የአገልግሎት አሰጣጡን በከፍተኛ ደረጃ ማሻሻል ትኩረት የሚሰጠው ሲሆን ፥ የኑሮ ውድነትን ማሻሻል በተመለከተ ርብርብ የሚደረግበት ማዕከል ሆኖ እንደሚቀጥልም ነው የተገለጸው፡፡

የከተማዋን ሰላምና ደህንነት የማረጋገጥ ስራ እንዲሁም ሌብነትና ስርዓት አልበኝነትን ማስተካከል ትኩረት የሚሰጠው እና ህዝቡን በማሳተፍ የሚከናወን እንደሆነ ነው በግምገማው የተነሳው፡፡

የስራ እድል ፈጠራ ስራም ሌላው የትኩረት ማእከል እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን ፥ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን የማጠናቀቅና አማራጭ የቤት አቅርቦት ሞዳሊቲን ማስፋትና የመፈፀም አቅም መገንባትም በትኩረት እንደሚታዩ ነው የተገለጸው፡፡

ህብረተሰቡን በየደረጃው በተለያዩ አጀንዳዎች ማወያየት እና ከህዝቡ ጋር ተቀራርቦ መስራት እንዲሁም የተጀመረው የከተማ ግብርና ስራን አጠናክሮ መቀጠል እና 4ኛ ዙር የአረንጓዴ አሻራ ስራን ከተቋማት ጀምሮ በተደራጀ መንገድ መፈፀም የቀጣይ ጊዜያት አቅጣጫ ሆኖም ተቀምጧል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.