Fana: At a Speed of Life!

በምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል በተለይም በአፋር ክልል እየተገነቡና በቀጣይም  የሚዘረጉ  የመንገድ ልማት ዙሪያ ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 15 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በምስራቁ የኢትዮጵያ ክፍል በተለይም በአፋር ክልል እየተገነቡና በቀጣይም  የሚዘረጉ  የመንገድ ልማት መርሃ-ግብር ፣ የክልሎች ሚና እና ተሳትፎ ላይ ያተኮረ የውይይት  መድረክ  በሰመራ ከተማ ተካሄደ።

በውይይት መድረኩ ላይ  የአፋር ክልል  ርዕሰ መስተዳድር  አቶ አወል አርባ  የትራንስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ ፣ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን  ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሃብታሙ ተገኘ ፣ የኢመባ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች  እና የክልል የስራ አመራሮች ተገኝተዋል።

በመድረኩ ላይ የቀጣይ የአስር አመታት የኢትዮጵያ የመንገድ  መሪ እቅድ ዋና ዋና  ይዘትን የዳሰሰ ሰነድ  ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል።

ከባለፋት አመታት የመንገድ መርሃ -ግብሮች አተገባበር የነበሩ ውስንነቶችን በመለየት፣ ቀጣይ የሀገራችን የመሰረተ ልማት አውታር ሊኖረው የሚችለውን ጸጋዎች አሟጦ ለመጠቀም በሚያስችል መልኩ በጥልቀት መዘጋጀቱ በሰነዱ  ተመላክቷል።

ከዚህ አኳያ በመንገድ ግንባታ ሂደት ውስጥ ክልሎችን በአደረጃጀት ፣በመዋቅር ፣በአቅም ግንባታ አሳድጎ የመሰረተ ልማት አውታሩን በከፋተኛ ደረጃ ለማሳለጥ መሪ እቅዱ የጎላ ሚና እንዳለው በዝርዝር አስቀምጧል።

አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታና  በቀጣይ ከሚኖረው ሰፊ የመሰረተ ልማት ግንባታ የክልሎችን አቅም አሳድጎ ፣ቀጥተኛ የመንገድ ግንባታ እና ፕሮጀክቶችን ወደ ማስተዳደር የሚያሸጋግር በመሆኑ አስቀድሞ የተዘጋጀው ሰነድ  ፋይዳው የጎላ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ አወል ተናግረዋል።

በእቅድ ግብአትነት ሊካተቱ ይገባቸዋል ያሏቸውን አንኳር ነጥቦችንም የክልሉ የስራ ሃላፊዎች አንሰተዋል።

እንዲሁም በቀጣይ ሊተኮርባቸው በሚገቡ አጀንዳዎች ላይም ተወያይተዋል።

ኢንጂነር ሃብታሙ ተገኘ በበኩላቸው መሪ እቅዱ ክልሎችን በቀጥታ የመንገድ የመሰረተ ልማት ግንባታ ባለቤትና ተቆጣጣሪ በማድረግ ፣ አንድ ተቋም ላይ ተንጠልጥሎ የቆየውን ከፍተኛ የስራ ጫናን ወደ ክልሎች የሚያጋራ ነው ብለዋል ።

ይህም የሀገሪቱን የመንገድ አውታር በከፍተኛ ፍጥነትና ጥራት ለመከወን እንደሚያስችል አብራርተዋል።

የትራንስፖርት ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ካሳሁን ጎፌ በበኩላቸው መሪ እቅዱ በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ብልጽግናዎችን ለማጎናጸፍ ሚናው የለቀ እንደሆነ ገልጸዋል።

መንግስት በመስኩ  የክልሎችን አቅም ለመገንባት የሚያስችል መጠነ ሰፊ ስራዎችን እንደሚያከናውንም አረጋግጠዋል።

በተለይም የክልሎችን ሚና እና ሃላፊነት በግልጽ አስቀምጦ ይበልጥ የሚያጠናክር በመሆኑ፣ የነበሩ ውስንነቶችን በመቅረፍ ለሀገራዊ የመንገድ የመሰረተ ልማት ግንባታ ፋይዳው ዘርፈ ብዙ እንደሆነም መናገራቸውን ከባለስልጣኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታሉ።

ይህን ተፈጻሚ የሚያደርጉ ዝርዝር የፖሊሲና የህግ ማእቀፍችን መንግስት እያዘጋጀ እንደሆነም  የስራ ሀላፊዎቹ ገልጸዋል።

በዚሁ በሰመራ ከተማ በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ በተለይሞ በክልሉ በቀጣይ ወደ ግንባታ የሚሸጋገሩ የመንገድ ፕሮጀክቶች በዝርዝር ቀርበዋል።

እንዲሁም በግንባታ ላይ የሚገኙ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች አፈጻጻምና እያጋጠማቸው ያሉ ተግዳሮቶች ላይም ምክክር ተካሂዶል።

በተለይም ከወሰን ማስከበር ጋር ተያይዞ ያጋጠሙ ችግሮችን ይበልጥ ተናቦ ለመፍታት የጋራ አቅጣጫን አስቀምጠዋል።

አቶ አወል አርባ በቀጣይ ለሚተገበሩ እቅዶችና ማሻሻያዎች እንዲሁም አሁን በግንባታ ላይ ለሚገኙ ፕሮጀክቶች መጠናቀቅ ክልሉ ክትትልና ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.