Fana: At a Speed of Life!

ጎጃምን ሲያውክ የነበረው ጽንፈኛ ሀይል ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል – ጀኔራል አበባው ታደሰ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጎጃምን ሲያውክ የነበረው ጽንፈኛ ሀይል ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበታል ሲሉ የጦር ሃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀኔራል አበባው ታደሰ ገለጹ።

ጀኔራል አበባው ታደሰ ዛሬ በፍኖተ ሰላም ከተማ ከጎጃም ኮማንድፖስት ከፍተኛ አመራሮች ጋር ውይይት አድርገዋል።

ጎጃምን ሲያውክ የነበረው ጽንፈኛ ሀይል ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት የገለጹት ጀኔራል አበባው፤ የጎጃም ኮማንድፖስት ጽንፈኛውን ሀይል በሚገባ መቶታል ሲሉ ተናግረዋል።

ሠራዊታችን የሕዝቡን ሰላም ለማምጣትና ሕግ ለማስከበር ባደረገው ስምሪት ጽንፈኛው ቆም ብሎ የመዋጋት ቁመናውን አጥቷል ነው ያሉት።

ዘራፊው ቡድን በህዝቡ ላይ ባደረሰው ግፍ ከህዝብ ተነጥሏል በማለት ገልጸው÷ በደረሰበት ሽንፈት ሀይሉ ተመናምኗል ፣ የሎጂስቲክ አቅሙ ተዳክሟል፣ በውስጡ በገጠመው ችግርም ተሰነጣጥቋል፣ ተራ ሽፍታ ሆኗል፣ አደረጃጀትም የለውም ብለዋል።

በዚህም ወደ ሽብር ስራ መግባቱን ገልጸው፤ የሀገር መከላከያ ሰራዊቱ በአሁኑ ሰዓት በተግባር የተፈተነ ግዳጅ የመፈጸም አቅሙም የዳበረ መምጣቱንም አንስተዋል፡፡

ሠራዊቱ ከፍተኛ ጽናት ያለው፣ የውጤት የበላይነት የያዘ፣ በአስተሳሰብም በተግባርም ተፈትኖ የጠነከረ ሀይል ሊሆን መቻሉንም ተናግረዋል።

የጎጃም ኮማንድ ፖስት በተሰማራበት ቀጠና የተወጣው ተልዕኮ የጽንፈኛውን ሀይል በእጅጉ ያዳከመ፣ ዘራፊውን ቡድን ከሕዝብ በመነጠል የልማት እና ማህበራዊ አገልግሎት ተቋማት ስራ እንዲጀምሩ ያስቻለ ውጤታማ ግዳጅ መወጣቱን አረጋግጠዋል።

ኮማንድፖስቱ ያገኘውን ድል አስጠብቆ ግዳጁን ሙሉ በሙሉ ማጠናቀቅ ይገባዋል ማለታቸውን ከመከላከያ ሠራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.