Fana: At a Speed of Life!

መሬት እናሰጣለን በሚል ሙስና ተቀብለዋል የተባሉ የመዲናዋ የቀድሞ ሠራተኞች እስከ 13 ዓመት በሚደርስ እስራት ተቀጡ

 

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ባዶ መሬት እናሰጣለን በማለት ከ10 ሚሊየን ብር በላይ ሙስና ተቀብለዋል የተባሉ የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር የቀድሞ ሠራተኞች በ6 እና 13 ዓመት ጽኑ እስራትና በገንዘብ እንዲቀጡ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ውሳኔ ሰጠ።

ተከሳሾቹም የአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 የግንባታ ቁጥጥር ባለሙያ ፍቅረሥላሴ ታደለ እና የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ቅሬታ ሰሚ የቀድሞ ዳይሬክተር ታምራት እስጢፋኖስ ናቸው።

በዚሁ መዝገብ በ3ኛ ተራ ቁጥር ተካትተው ክስ ቀርቦባቸው የነበሩት የየካ ክፍለ ከተማ መሬት አሥተዳደር የመብት ፈጠራ ቡድን መሪ ዘውዱ ደገፋን ፍርድ ቤቱ ቀደም ብሎ በብይን ነጻ ማለቱ ይታወሳል፡፡

የፍትሕ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት ጀነራል ተከሳሾቹን በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1) ሀ እና ለ የሙስና አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 32 (2) የተመለከተውን ድንጋጌ ተላልፈዋል በማለት በ2015 ዓ.ም የማታለል ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ አቅርቦባቸው ነበር።

በክስ ዝርዝሩም 1ኛ ተከሳሽ የዐቃቤ ሕግ ምስክር የሆኑ የግል ተበዳይን በማግኘት እራሱን የከተማ አሥተዳድሩ የመሬት አሥተዳደር ካቢኔ ነኝ በማለት አሳሳች ነገሮችን በመግለጽ የግል ተበዳይ እንዲያምነው በማድረግ ግለሰቡን ጥቅምት 2 ቀን 2015 ዓ.ም በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 05 ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ቅጥር ጊቢ በመጥራት ከ2ኛ ተከሳሽ ጋር በመሆን በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 አራራት ሆቴል ጀርባ 5 ሺህ ካሬ ሜትር ባዶ መሬት እናሰጣለን በማለት አስቀድመው 25 ሚሊየን ብር ሙስና ገንዘብ ከጠየቁ በኋላ በቅድሚያ ለፕሮጀክት ማሠሪያ 250 ሺህ ብር በቼክ መቀበላቸው ተጠቅሷል።

እንዲሁም ጥቅምት 8 ቀን 2015 ዓ.ም የግል ተበዳይ የነዋሪነት መታወቂያ ኮፒ፣ ፓስፖርት ኮፒ፣ የባንክ ስቴትመንታቸውን ኮፒ እንዲሰጧቸው በማድረግ ጥቅምት 24 ቀን 2015 ዓ.ም 2 ሚሊየን ብር በቼክ መቀበላቸው በክሱ ተመላክቷል፡፡

በተመሳሳይ መልኩ ከሁለቱ የግል ተበዳዮች 10 ሚሊየን 250 ሺህ ብር ተቀብለዋል ሲል ዐቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል።

በተጨማሪም ለሜሪዲያን ሆቴል ባለቤት በሆቴሉ ስም በተመዘገበ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ላይ ተጨማሪ ካሬ ሜትር በማካተት የመከነው ካርታቸው እንደሚስተካከልላቸው በመግለጽ፤ የተለያዩ ሐሰተኛ ሠነዶችን ለግል ተበዳይ ማሳየታቸውን ሠነዶቹም በ1ኛ ተከሳሽ መኖሪያ ቤትና 2ኛ ተከሳሽ በሚያሽከረክረው ተሽከርካሪ ውስጥ በብርበራ መገኘቱን ጠቅሶ ዐቃቤ ሕግ ዝርዝር ክስ አቅርቦባቸው እንደነበር ይታወሳል።

ክሱ ለተከሳሶቹ ከደረሳቸው በኋላም የዋስትና መብት እንዲፈቀድላቸው ያቀረቡት ጥያቄ ከተከሰሱበት ድንጋጌ አንጻር ውድቅ ተደርጎ በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ተደርጓል።

የወንጀል ድርጊቱን አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው የሰጡትን የዕምነት ክህደት ቃል ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ የሠነድና የሰው ማስረጃ አቅርቧል።

ፍርድ ቤቱም መርምሮ ተከሳሾቹ በተከሰሱበት ድንጋጌ እንዲከላከሉ ብይን የሰጠ ቢሆንም፤ በተገቢው መከላከል አለመቻላቸው ተገልጾ የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፎባቸዋል።

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየት ዛሬ በዋለው ቀጠሮ 1ኛ ተከሳሽ የአራዳ ክ/ከ ወረዳ 6 የግንባታ ተቆጣጣሪ ባለሙያ የነበረውን ፍቅረስላሴ ታደለን በዕርከን 31 መሰረት በ13 ዓመት ጸኑ እስራትና በ5 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ወስኗል።

2ኛ ተከሳሽ የቀድሞ የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ቅሬታ ሰሚ ዳይሬክተር ታምራት እስጢፋኖስን በዕርከን 23 መሰረት በ6 ዓመት ጽኑ እስራትና በ2 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ወስኗል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.