Fana: At a Speed of Life!

በሳዑዲ ዓረቢያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከ11 ሺህ በላይ የቤት ሰራተኞችን ሰነድ ተቀብሎ ማስተናገዱን አስታወቀ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 18 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በሳዑዲ ዓረቢያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ኢትዮጵያ እና ሳዑዲ ዓረቢያ በተፈራረሙት የሰራተኛ እና አሰሪዎች ስምምነት መሰረት ባለፉት ስምንት ወራት ከ11 ሺህ በላይ የቤት ሰራተኞችን ሰነድ ተቀብሎ ማስተናገዱን አስታወቀ።

በሳዑዲ ዓረቢያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር አብዱላዚዝ አህመድ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥ ሰነዳቸው ከታየላቸው ሰራተኞች መካከል አብዛኛዎች ስራ ጀምረዋል።

በሳዑዲ ያለውን የሰራተኛ ፍላጎት መሰረት በማድረግም ለኢትዮጵያውያን ተጨማሪ የስራ እድል ለማመቻቸት ኤምባሲው ጅዳ ከሚገኘው ቆንስላ ፅህፈት ቤት ጋር በመሆን እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም ተናግረዋል።

በህጋዊ መንገድ ወደ ሪያድ እየገቡ ያሉ ሰራተኞች አዲስ አበባ ውስጥ ስልጠና ያገኙ በመሆናቸው ከአሁን በፊት ያጋጥማቸው የነበሩ ችግሮችን በቀላሉ ማለፍ የሚችሉ ናቸው ተብሏል።

አምባሳደር አብዱላዚዝ በህጋዊ መንገድ ሰራተኞችን ወደ ሪያድ ከማስገባት ጎን ለጎን ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል ከሪያድ ባለስልጣናት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።

በስላባት ማናዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.