Fana: At a Speed of Life!

በሴናተር ክሪስ ኩንስ ከሚመራው ልዑክ ጋር የተደረገው ውይይት ገንቢ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 13 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከሴናተር ክሪስ ኩንስ ከሚመራው የአሜሪካ ልዑካን ጋር ያደረጉት ውይይት ገንቢ እንደሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ አስታወቁ።

አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ከትናንት በስቲያ አዲስ አበባ የገባው በሴናተር ክሪስ ኩንስ የሚመራው የአሜሪካ የልዑካን ቡድን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መወያየቱንና ውይይቱም ገንቢ እንደነበር ከኢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ አስታውቀዋል።

በውይይቱ አቶ ደመቀ መኮንን በአሜሪካ መንግሥት በኩል በትግራይ በተካሄደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ዙሪያ ያለውን ውዥንብር ማጥራት የሚያስችል በቂ ማብራሪያ መስጠታቸውን ገልጸዋል።

የሕግ ማስከበር ዘመቻው መነሻው ምን እንደነበር፣ ሂደቱ ምን እንደሚመስል እና የተገኘው ውጤት ምን መልክ እንዳለው አቶ ደመቀ በዝርዝር ለልዑካን ቡድኑ በዝርዝር ማስረዳታቸውንም ነው የገለጹት።

በአሁኑ ሰዓት ትግራይን መልሶ ለማቋቋም ምን እየተሰራ እንደሆነም በቂ መረጃ መስጠታቸውን አመላክተዋል።

በተለይ የኢትዮጵያ መንግሥት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሰብአዊ ድጋፍ ሰጪ ወገኖች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ወደ ትግራይ ገብተው ድጋፎችን መስጠት እንደሚችሉ፣ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችም በዚያው ልክ እውነታውን መታዘብ እንደሚችሉ መፍቀዱንና ይህም ተግባራዊ እየሆነ እንደሚገኝ ማስታወቃቸውንም ጠቁመዋል።

በተጨማሪም በአካባቢው ይፈጸማል ተብሎ ለሚነሳው የሰብአዊ መብት ጥቃትን፣ መንግሥት ያለ ምንም ማመንታት ወንጀለኞችን ወደ ሕግ አቅርቦ የማስጠየቅ፣ አጣርቶ የመቅጣት አቅጣጫ እንደሚከተል ለልዑካኑ ማሳወቃቸውንም አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ሉአላዊ ሀገር እንደመሆኗ መጠን በግዛቷ ውስጥ ለምታካሂደው ማንኛውም ዓይነት የሕግ ማስከበር ዘመቻ ጣልቃ ገብነትን እንደማትሻ አቶ ደመቀ በዚህ ወቅት ጠቁመዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ሆነ የአሜሪካ መንግሥት እንደ ወዳጅ መንግሥት በሀገሪቱ እየሆነ ስላለው ነገር ትክክለኛውን ነገር እንዲያጤነው፣ እንዲረዳውና አብሮ ለመስራትና ያልተስተካከሉ ነገሮችም ካሉ ለማስተካከል በኢትዮጵያ በኩል ፍላጎት መኖሩንም ለልዑካን ቡድኑ መነገሩን ገልጸዋል።

ሱዳን ኢትዮጵያ ላይ ያደረገችው የድንበር ወረራ ሉአላዊነቷን የሚጋፋ መሆኑን፣ ሀገሪቱ ካለችበት እብሪት ወጥታ ወደ ሰላማዊ መንገድ እንድትመጣ አሜሪካ ጫና እንድታሳድርም አቶ ደመቀ መጠየቃቸውን ጠቁመዋል።

የህዳሴ ግድብ ድርድርን በተመለከተ በአፍሪካ ህብረት በኩል የተጀመረው የሦስቱ ሀገራት ድርድር እንዲቀጥል ኢትዮጵያ ጽኑ ፍላጎት እንዳላት ማሳወቃቸውንም አውስተዋል።

ሴናተር ግሪስ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ የአሜሪካ ቁልፍ አጋር መሆኗን አስታውቀው፣ በሀገሪቱ የሚደረግ ማንኛውም አሉታዊ ጉዳይ አሜሪካን እንደሚያሳስባት ጠቁመዋል።

በትግራይ ክልል እየተካሄደ ያለው የሰብአዊ እርዳታ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መጠየቃቸውን ኢፕድ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.