Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል በ2 ነጥበ 3 ቢሊየን ብር የሚከናወነው 2ኛው አንድ ቋት ዋን ወሽ ፕሮግራም ተጀመረ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 11 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል በ2 ነጥበ 3 ቢሊየን ብር የሚከናወነው 2ኛው አንድ ቋት ዋን ወሽ ፕሮግራም ተጀመረ።

በፕሮግራሙ ላይ የክልሉ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ልማት፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ እንዲሁም የትምህርት ቢሮ አመራሮችን ጨምሮ የወረዳ፣ የዞን እና የክልል ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

የክልሉ ውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ልማት ቢሮ የመጠጥ ውሃ ዳይሬክተር አቶ አስራት ካሴ፥ ዋን ወሽ ፕሮግራም በክልሉ የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋንን ለማረጋገጥ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።

2ኛው ምዕራፍ ከ2012 እስከ 2016 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ ወደ ትግበራ መግባቱንም አስታውሰዋል።

በዚህም መሰረት በክልሉ በሚገኙ 90 ወረዳዎች እና 20 አነስተኛ ከተሞች 360 መለስተኛ ጥልቅ ጉድጓድ በመቆፈር 1 ሺህ 394 አነስተኛ የገጠር ተቋማትን ተጠቃሚ ለማድረግ ዕቅድ መያዙን ገልፀዋል።

በተመሳሳይ ለ320 የጤና እና 360 የትምህርት ቤት ተቋማት የተሻለ የንጹህ መጠጥ ውሃ በማቅረብ፥ የተሠሻሻለ የፍሳሽ አወጋገድና ንጽህና አገልግሎት ለመስጠት መታቀዱንም ጠቅሰዋል።

መድረኩ የ2ኛውን ምዕራፍ የአንድ ቋት ዋንወሽ አላማን፥ ሃላፊዎች፣ የፖለቲካ አመራሮች እና ሙያተኞች በአግባቡ ተረድተው በቁርጠኝነት እንዲፈጽሙ ግንዛቤ ለመፍጠር ያለመ መሆኑም ተገልጿል።

ለፕሮግራሙ ማስፈፀሚያም 2 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር መመደቡንም ነው ዳይሬክተሩ የተናገሩት።

በናትናኤል ጥጋቡ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.