Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል ባለፉት አምስት አመታት ከወጪ ንግድ ከ92 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘት መቻሉ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ባለፉት አምስት አመታት 28 የኢንዱስትሪ መንደሮችን ወደ ስራ በማስገባት ከ92 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘት መቻሉን የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ገለጸ።

የኢትዮጵያ ታምርት አካል የሆነው የኢንቨስትመንት የውይይት ፎረም በኮምቦልቻ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በውይይት መድረኩ የአማራ ክልል አፈ ጉባዔ ፋንቱ ተስፋየን ጨምሮ የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል።

የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሃላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ እንደተናገሩት ፥ በክልሉ 28 የኢንዱስትሪ መንደሮችን ወደ ስራ በማስገባት ከ75 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ከመፍጠር ባሻገር ባለፉት 5 ዓመታት ከ92 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘት ተችሏል።

በክልሉ የሚገኙትን ከ3 ሺህ 600 በላይ አምራች ኢንዱስትሪዎች በቀጣይ ችግራቸውን በመፍታትና እሴት በመጨመር ወደ ውጭ ገበያ ለመላክ ቀጣይ አቅጣጫ መቀመጡን ተናግረዋል።

የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ መሀመድ አሚን በበኩላቸው ፥ ከተማዋ ከ860 በላይ ሄክታር መሬት ለኢንቨስትመንት ማቅረቧን ጠቅሰው ቀጣይ በዘርፉ የሚታየውን ማነቆ ለመፍታት ይሰራልም ነው ያሉት።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ባለፉት 9 ወራት በኮምቦልቻ ከተማ ከሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎች ከ19 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱ ተገልጿል።

በውይይት ፎረሙ ባለሀብቶች የተገኙ ሲሆን ፥ ለማምረት ማነቆ የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት እያደረጉ ነው።

በከድር መሀመድና አንድነት ናሁሰናይ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.