Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ስርጭት ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን የጤና ባለሙያዎች ገለፁ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 20፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል አሉ የጤና ባለሙያዎች።

ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉ የጤና ባለሙያዎች ህብረተሰቡ ቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል እያሳየ ያለው መዘናጋት ደግሞ ከፍተኛው ድርሻ ይዟል ብለዋል።

በቫይረሱ ተይዘው ያገገሙ ሰዎችም ድጋሚ እየተያዙ በመሆኑ እንደማንኛውም ሰው ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባቸውም ባለሙያዎቹ አሳስበዋል።

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የኮቪድ ህክምና ማእከል ዳይሬክተር ዶክተር ደሳለኝ ቀነኢ የቫይረሱ ስርጭት ከዚህ ቀደም ከነበረው በላይ እንደሆነ ነው የሚያነሱት።

በቫይረሱ ተጠርጥረው ምርመራ ከሚደረግላቸው ወስጥ ከ10 በመቶ በላዩ፣ ምልክት አሳይተው ከሚመረመሩት ከ65 እስከ 70 በመቶ ያህል ቫይረሱ እየተገኘባቸው መሆኑን ነው ዶክተር ደሳለኝ የነገሩን።

ይህ ደግሞ የቫይርሱ ስርጭት አስጊ መሆኑን የሚያሳይ ነው።

በኢትዮጰያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የኮቪድ መከላከል ማእከል ውስጥ የሚሰሩት እና የህክምና ባለሙያው አቶ የኋላው ጌታሁን ሀሳበም ይሀንኑ የሚያጠናከር ሀሳብ ተናግረዋል።

ቫይረሱን ለመከላከል የተለያዩ መመሪያዎች እና ፕሮቶኮሎች በመንግስት በኩል እየወጡ ቢሆንም ትግበራው ላይ ግን ክፍተቶች እየተስተዋሉ ነው ይላሉ።

አቶ የኋላው እንደሚሉት በህግ ደረጃ የተቀመጡ መመሪያዎችም እየተተገበሩ አይደለም።

አሁን ላይ በቫይረሱ የሚያዙት ሰዎች ቁጭር ከመጨመሩ በላይ በፅኑ የሚታመሙት እና ህይወታቸው የሚያልፍ ሰዎችም ቁጥር በየቀኑ እያሻቀበ መሆኑም ተናግረዋል፡፡

የጤና ባለሙያዎቹ እንደሚሉት የመመርመር አቅማችን ስላነሰ በቫይረሱ የሚያዘው ሰው ትንሽ እንደሆነ የሚያስቡ ሰዎች አሉ ።

በየእለቱ ከሚያዩት እና ካላቸው መረጃ በመነሳት የሞት ቁጥር እየጨመረ ነው ብለዋል፡፡

በየትኛውም የእድሜ ክልል ያሉ ሰዎችም በየቀኑ የዚህ ክፍ እጣ እየደረሰባቸው ይገኛል ነው ያሉት ባለሙያዎቹ፡፡

በቫይረሱ ተይዘን ባንሞት እንኳን ዘላቂ የጤና እክል እንደሚያመጣ ነው ጥናቶች እያሳዩ ያሉ።

ሳንባ፡ኩላሊት እና የመሳሰሉት የአካል ክፍሎቻችን ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርሰው ኮቪድ በቫይረሱ ተይዘው ያገገሙትንም ድጋሚ እያጠቃ ይገኛል።

ከዚህ ቀደም በቫይረሱ ተይዘው ያገገሙ ሰዎች ድጋሚ እየተያዙ እንደሆነ እና ወደ ማእከላቸው የመጡ ሪፖርቶችም መኖራቸውን ነው ዶክተር ደሳለኝ የነገሩን።

አሁን ላይ ያገገሙ ሰዎችም ድጋሚ እየተያዙ በመሆኑ የጥንቃቄ ጉድለቱ ሰፊ መሆኑን የሚያሳይ ነው የሚሉት የጤና ባለሙያዎቹ ሁሉም ህብረተሰብ መዘናጋቱን እንዲያቆምም አሳስበዋል።

በተለይም ትምህርት ቤቶች፣ የሀይማኖት ቦታዎች አና መሰል ሰዎች በብዛት የሚገለገሉባቸው ስፍራዎች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባም አንስተዋል።

እንደ ሀገር የተጀመረው “እንድናገለግልዎ ማስክዎን ያድርጉ” እና መሰል የጥንቃቄ ዘመቻ ስራዎችም ተጠናክረው መቀጠል ከቻሉ ውጤት ሊያመጡ እንደሚችሉም ነው ዶክተር ደሳለኝ እና አቶ የኋላው የተናገሩት።

ዙፋን ካሳሁን

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.