Fana: At a Speed of Life!

በክረምቱ ወቅት በአንዳንድ አካባቢዎች ከባድ ዝናብና ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊከሰት ይችላል – የሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ አንዳንድ አካባቢዎች ከባድ ዝናብና ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊከሰት እንደሚችል አስጠነቀቀ፡፡
በኢንስቲትዩቱ የአየር ሁኔታና የአየር ጸባይ ትንበያ ዳይሬክተር ወይዘሮ ጫሊ ደበሌ እንደገለጹት÷ ከደቡባዊ ንፍቀ ክበብ ወደ አገራችን የሚገባው እርጥበት አዘል አየር ካለፉት ሳምንታት በበለጠ በቀጣዮቹ ሳምንታት ሊጠናከር ይችላል፡፡
በመሆኑም የጎርፍ አደጋ ሥጋት ያለባቸው አካባቢዎች ላይ አደጋ እንዳይፈጠር ከወዲሁ የመከላከል ሥራ ማከናወን እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በተለይ ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ በሆኑ ወንዞችና ተዳፋታማ አካባቢዎች የሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች÷ የተጠናከረ የጥንቃቄ እርምጃ ሊወስዱ እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት፡፡
በአንዳንድ ቦታዎች ላይ እርጥበት አዘል አየር በአጭር ጊዜ ተጠናክሮ ከባድ ዝናብ በመፍጠር ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊያስከትል እንደሚችል ጠቁመው÷ በተለይ በከፍተኛ ቦታዎችና፣ በደጋ አካባቢ የሚዘንበው ዝናብ በዝቅተኛ አካባቢዎች ላይ የጎርፍ አደጋ ሊያስከትል ስለሚችል አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
በመካከለኛ እና ሰሜን ምስራቅ የአገሪቱ ክፍሎች እና በዝቅተኛ ቦታዎች ላይም በአጭር ጊዜ የሚጥለው ዝናብ ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊያስከትል ስለሚችል መጠንቀቅ እንደሚገባ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
አልፎ አልፎ የሚያጋጥመው የመብረቅ አደጋ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ህብረተሰቡ የራሱን ጥንቃቄ እንዲያደርግም ጥይቀዋል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.