Fana: At a Speed of Life!

በኮሎራዶ ግዛት የጁንታው ቡድን በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመውን ክህደት የሚያወግዝ  ሰልፍ ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 1፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)በኮሎራዶ ግዛት ዴንቨር ከተማ ኢትዮጵያውያን እና  ኤርትራውያን የጁንታው ቡድን በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመውን ክህደት የሚያወግዝ  ሰላማዊ ሰልፍ በኮሎራዶ ግዛት መንግስት ዋና ጽህፈት ቤት ስቴት ካፒቶል አደባባይ አካሂደዋል።

ሰልፉ የተካሄደው በኮሎራዶ የኢትዮጵያውያን ኮሚዩኒቲ፣ የኢትዮጵያ አሜሪካውያን የሲቪክ ካውንስል፣ የኢትዮጰያ ወዳጆች እና ሌሎች የኢትዮጰያውያን መብቶች ተከራካሪ ድርጅቶች  አስተባባሪነት መሆኑ ተመላክቷል።

በዚህም ሰልፍ ከ500 በላይ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን የዳያስፖራ አባላት የተሳተፉ ሲሆን÷ የህወሓት ወንጀለኛ ቡድን በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመውን የክህደት ጥቃት አውግዘዋል።

የዓለም ዓቀፉ ህብረተሰብ ሁኔታውን በአግባቡ እንዲገነዘብ እና የወንጀል ቡድኑን ደጋፊዎች ከሚያበረታቱ አቋሞች እንዲታቀብም ጥሪ አቅርበዋል።

ሰልፈኞቹን በመወከል የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ ተወካይ፣ የኤርትራ ኮሚዩኒቲ ተወካይ እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ማህበራት ተወካዮች  እና ሌሎች ታዋቂ ግለሰቦች ንግግር አድርገዋል።

በተለይም የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ተወካዮች በንግግራቸው ሁለቱ ሀገሮች የደረሱበትን የሰላም እና የዕርቅ ሂደት ለማጨናገፍ የህወሃት ቡድን የሸረበው ሴራ በህግ ማስከበር ዕርምጃው መክሸፉ እጅግ ያስደሰታቸው ተግባር መሆኑን  ጠቅሰዋል።

አያይዘውም የሁለቱ አገሮች ሰላማዊ ግንኙነት እንዲዳብር ዳያስፖራው የራሱን ሚና እንዲጫወት ጥሪ አቅርበዋል።

በተጨማሪም ሰልፈኞቹ የህወሃት ቡድን ለ27 ዓመታት በኢትዮጵያ ወንድማማች ብሄሮች እና ብሄረሰቦች መካከል ሊዘራ የሞከረው የጥላቻ እና የጥርጣሬ መርዝ የከሸፈ መሆኑን እና ይህንኑ የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ በማውገዝ፣ ህብረታቸውን ይበልጥ ለማጠናከር እና የትህነግ ወጥመድ ሰለባ ላለመሆን ቁርጠኛነታቸውን አረጋግጠዋል።

በመጨረሻም ሰልፈኞቹ ለተመራጭ የሴኔት እና የኮንግሬስ አባላት እንዲሁም ለየከተሞቹ ከንቲባ ጽህፈት ቤቶች እና ለሌሎች የአሜሪካ የፖለቲካ ተቋማት የአቋም መግለጫዎቻቸውን እና ደብዳቤዎቻቸውን በማስገባት ሰልፉን ማጠናቀቃቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.