የኖክ ነዳጅ ማደያ ስራ አስኪያጅን በማስፈራራት ገንዘብ የተቀበሉ በእስራትና በገንዘብ ተቀጡ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኖክ ነዳጅ ማደያ ስራ አስኪያጅን በወንጀል ትፈለጋለህ በማለት አስፈራርተው ገንዘብ ተቀብለዋል ተብለው ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል ሙስና ወንጀል የተከሰሱ አምስት ግለሰቦች እስከ 13 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራትና በገንዘብ እንዲቀጡ ተወሰነ።
የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወንጀል ችሎት የቅጣት ውሳኔ የወሰነባቸው ተከሳሾች 1ኛ ጫላ መገርሳ፣ ለሊሳ በቀለ፣ ዳዊት ጉደታ፣ ዮሃንስ ደረጄ እና ብርቱካን ለታ ናቸው።
የክልሉ ፍትህ ቢሮ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ተከሳሾቹ የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 ንዑስ ቁጥር 1 ሀ ና ለ እንዲሁም የሙስና ወንጀልን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9 ንዑስ ቁጥር 2 ስር የተመላከተውን ድንጋጌ እና በአዋጅ ቁጥር 780/2005 አንቀጽ 29/1 ስር የተመላከተውን ድንጋጌ መተላለፋቸውን ጠቅሶ በ2015 ዓ.ም ክስ መስርቶባቸው ነበር።
በክሱ ዝርዝር ላይ እንደተመላከተው፤ ከ1ኛ እስከ 4ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች ተገቢ ያልሆነ ብልጽግና ለማግኘት ወይም ለሌሎች ለማስገኘት በማሰብ በመጋቢት 19 ቀን 2015 ዓ.ም ከቀኑ 11:00 ሰዓት ላይ በሸገር ከተማ ገፈርሳ ክፍለ ከተማ አካባቢ በሚገኝ የኖክ ነዳጅ ማደያ ስራ አስኪያጅ የሆነ የግል ተበዳይን የፀጥታ አካላት ነን፣ በወንጀል ትፈለጋለህ በማለት መንገድ ላይ በማስቆም ከውጭ ወደ ውስጥ እንዳይታይ አድርገው በስቲከር ሸፍነው ወደአዘጋጁት የቤት መኪና ውስጥ በማስገባት ወደ መልካ ናኖ ክ/ከ አንፎ ወደ ተባለ አካባቢ ወስደውታል።
ከዚህም በኋላ የሞተ ሰው ፎቶ ለግል ተበዳዩ በማሳየትና በመሳሪያ በማስፈራራት ግማሽ ሚሊየን ብር እንዲያመጣና እንደሚለቁት በመግለጽ ገንዘቡን ካልከፈለ ደግሞ ወደ ጦር ኃይሎች እንወስድኃለን በማለት ገንዘብ እንዲከፍል መጠየቃቸውን ተከትሎ የግል ተበዳዩ በባንክ ሂሳቡ ውስጥ 100 ሺህ እንዳለው ገልጾ መልስ መስጠቱ በክሱ ተመላክቷል።
በዚህም ጊዜ 1ኛ ተከሳሽ ባለቤቱ በሆነችው በ5ኛ ተከሳሽ የባንክ ሂሳብ በሞባይል ባንኪንግ የግል ተበዳዩ 100 ሺህ ብር እንዲያዘዋውር ያደረገና ቀሪውን 400 ሺህ ብር እንዲያመጣ በማስጠንቀቅ የለቀቁት መሆኑን ዐቃቤ ሕግ በክሱ ላይ የጠቀሰ ሲሆን፤ በህገወጥ መንገድ የተገኘውን ገንዘብ ደግሞ 5ኛ ተከሳሽ ከአንደኛ ተከሳሽ ጋር በመሆን ምንጩን ለመደበቅ በማሰብ በተለያዩ መጠኖች ወጪ በማድረግ ለግል ጥቅም ያዋሉት መሆኑ በክሱ ዝርዝር ላይ ሰፍሯል።
ተከሳሾቹ ክሱ ከደረሳቸው በኋላ ድርጊቱን ክደው በመከራከራቸው ዐቃቤ ሕግ የሰው ምስክሮችን፣ አስረጂና ገላጭ የሰነድ ማስረጃዎችን ለችሎቱ አቅርቧል።
ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን መርምሮ ተከሳሾቹ በተከሰሱበት ድንጋጌ እንዲከላከሉ ብይን ቢሰጥም ተከሳሾቹ በተገቢው መከላከል ባለመቻላቸው የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፎባቸዋል።
ከዚህም በኋላ ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ሕግን ቅጣት ማክበጃ አስተያየትንና የተከሳሾቹ የቅጣት ማቅለያ አስተያየት በመያዝ 1ኛ ተከሳሽን በ13 ዓመት ጽኑ እስራትና በ3 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ወስኗል።
ከ2ኛ እስከ 4ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾችን ደግሞ እያንዳንዳቸውን በ7 ዓመት ጽኑ እስራትና በ3 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲቀጡ የወሰነው ፍርድ ቤቱ 5ኛ ተከሳሽን በሚመለከት በ1 ዓመት እስራትና በ1 ሺህ ብር ገንዘብ እንዲቀጡ ወስኗል።
በታሪክ አዱኛ