Fana: At a Speed of Life!

በ24 ሰዓት በተደረገ 3 ሺህ 747 የላብራቶሪ ምርመራ 9 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ተገኘባቸው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ በተደረገው 3 ሺህ 747 የላብራቶሪ ምርመራ 9 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ይህንን ተከትሎም በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 398 መድረሱን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ አስታውቅዋል።

ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ፥ እድሜያቸው ከ20 እስከ 49 ዓመት የሆኑ 8 ወንዶችና 1 ሴት ናቸው።

ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች መካከል 5 ሰዎች የውጭ የጉዞ ታሪክ ያላቸው፣ 2 ሰዎች በበሽታው ከተያዘ ሰዎች ጋር ግንኙነት ያላቸው፣ 2 ሰዎች ደግሞ የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክ እና በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት የሌላቸው መሆኑን አስታውቀዋል።

በዚህም ቫይረሱ በምርመራ ከተገኘባቸው ሰዎች ውስጥ 3 ሰዎች ከአዲስ አበባ ሲሆኑ፥ ከእነዚህም መካከል 2 ሰዎች በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት ያላቸው እንዲሁም 1 ሰው ደግሞ የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክ ያለው ነው።

2 ሰዎች ከአፋር ክልል (የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክ እና በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት የሌላቸው )፣ 1 ሰው በሶማሌ ክልል (ጅግጅጋ ልይቶ ማቆያ) ውስጥ የሚገኝ፣ 1 ሰው በትግራይ ክልል (የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክ ያለውና በማክድራ ለይቶ ማቆያ ያለ) እንዲሁም 2 ሰዎች አማራ ክልል (የውጭ የጉዞ ታሪክ ያላቸውና በመተማ ለይቶ ማቆያ ያሉ) መሆናቸውን ዶክተር ሊያ ገልፀዋል።

በሌላ በኩል በትናንትናው እለት 1 ሰው ከቫይረሱ ማገገማቸውንና በአጠቃላይ ከቫይረሱ ያገገሙ ሰዎች ቁጥር 123 መድረሱንም አስታውቀዋል።

ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ እስካሁን ለ69 ሺህ 507 ሰዎች ምርመራ የተደረገ ሲሆን፥ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ቫይረሱ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 398 ደርሷል።

አሁን ላይ 268 ሰዎች በህክምና ላይ ሲሆኑ፥ እስካሁንም 123 ሰዎች ከቫይረሱ አገግመዋል፤ የ5 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ፤ 2 ሰዎች ወደ ሀገራቸው ጃፓን መመለሳቸው ይታወሳል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.