Fana: At a Speed of Life!

ከህገ ወጦች የተሰበሰቡ ከ1 ሺህ 500 በላይ የሺሻ እቃዎች ተወገዱ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአራዳ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በተለያዩ ጊዜ ከህገ ወጦች የተሰበሰቡ የሺሻ እቃዎችን ማስወገዱ ተገለጸ።

የክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ለወንጀል መስፋፋት መንስኤ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ክትትል የማድረግ ስራውን አጠናክሮ ቀጥሏል ተብሏል፡፡

ሰሞኑን ባከናወነው የክትትል ስራም ህጋዊ የንግድ ፈቃድን ሽፋን በማድረግ ሺሻ ሲያስጨሱ በተገኙ ህገ ወጦች ላይ በተደረገ ፍተሻ ከ1 ሺህ 500 በላይ የሺሻ እቃዎችን መያዝ እንደቻለም ነው የተገለጸው፡፡

ከህገ ወጦቹ የተያዙት የሺሻ መጠቀሚያ እቃዎች ዛሬ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት መወገዳቸው ተጠቁሟል፡፡

በህገ ወጥ ተግባር ላይ ተሰማርተው የተገኙት ህጋዊ የንግድ ፍቃድን ሽፋን አድርገው ከሚንቀሳቀሱት መካከል ጫት መሸጫ ሱቆች እንዲሁም ሆቴልና ግሮሰሪ ቤቶች እንደሚገኙበት የክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ የወንጀልና የትራፊክ አደጋ ምርመራ ዲቪዚዮን ኃላፊ ምክትል ኮማንደር ዘሪሁን ተፈራ ገልፀዋል፡፡

ሺሻ በማስጨስ ህገ ወጥ ተግባር ላይ የተሰማሩትን ግለሰቦች ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ቤቶቹን የማሸግ እና በህግ ተጠያቂ የማድረግ ስራ ሰርተናል ብለዋል።

የማህበረሰቡ ድጋፍ ከፍተኛ እንደነበር በመግለጽ በቀጣይም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ቁጥጥሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

የክፍለ ከተማው የደንብ ማስከበር ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ሻምበል ኑርልኝ በበኩላቸው÷በህጋዊ ንግድ ፈቃድ ህገ-ወጥ ተግባር መፈፀም የህግ ተጠያቂነትን የሚያስከትል ነው ብለዋል፡፡

በመሰል ህገ-ወጥ ተግባር ላይ የተሰማሩ የንግድ ድርጅቶች ከህገ-ወጥ ተግባራቸው ሊታቀቡ እንደሚገባም ማሳሰባቸውን ከፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ህብረተሰቡ ለወንጀል መንስኤ የሆኑ ድርጊቶች ሲያጋጥሙት ለፀጥታ አካላት ጥቆማ የመስጠት ልምዱን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.