Fana: At a Speed of Life!

አሸባሪው ህወሓትን ለሀገርና ለህዝብ ስጋት በማይሆንበት ደረጃ የማክሰም የዘመቻው ግብ ሳይሳካ ትግሉ አይቆምም – የአማራ ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን

አዲስ አበባ፣ታህሳስ 14፣2014 (ኤፍ ቢሲ)  አሸባሪው ህወሓትን ለሀገርና ለህዝብ ስጋት በማይሆንበት ደረጃ የማክሰም ዘመቻው ግብ ሳይሳካ ትግሉ እንደማይቆም የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አስታውቋል።

ክልሉ በአሸባሪው ህወሓት ከደረሰበት ሰብዓዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳት መልሶ ለማቋቋምም የክልሉ መንግሥት ጥሪ አቅርቧል።

የአማራ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ስድስት ወራትን ያስቆጠረው የህልውና ዘመቻ በመከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል፣ ፋኖ እና ሚሊሻው ተጋድሎ ድል መመዝገቡን ገልፀዋል።

ስኬቱ በግንባር ከመፋለም ጀምሮ በፕሮፓጋንዳ፣ በመረጃና በሚዲያ እንዲሁም በተለያዩ መስኮች በታገሉ አካላት የመጣ ድል በመሆኑ የክልሉ መንግስት ለሁሉም ምስጋና አቅርቧል።

የችግር ጊዜ ጀግኖች ጎልተው የሚወጡበት እንደሆነ፤ ለዚህም ምስጋና የሚቀርብበትና የሚበረታቱበት መድረክ እየተዘጋጀ መሆኑን አቶ ግዛቸው ሙሉነህ በሰጡት መግለጫ አንስተዋል።

የጦርነቱ ግብ ሆኖ የተቀመጠው አሸባሪው ህወሓትን ዳግም የኢትዮጵያ እና የአማራ ህዝብ ስጋት በማይሆንበት ደረጃ ማድረስ መሆኑን ገልፀው ከዚህ አንፃር በርካታ ስራዎች በመቅረታቸው የክልሉ መንግሥት እስከ ድሉ ፍፃሜ ድረስ አበክሮ እንደሚሠራም ገልፀዋል።

በወረራ የተፈናቀሉ ወገኖችን እና የወደሙ ተቋማትን መልሶ የማቋቋምና የመገንባት ሥራ እንደሚጠበቅ የክልሉ ምክር ቤት አቅጣጫ ማስቀመጡን ጠቅሰው፥ የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት፣ ባለሀብቶች፣ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና ሌሎችም ርብርብ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

ከሰሞኑ በብዛት እየተነሳ ባለው የድርድር ጉዳይ ዙሪያ በሰጡት አስተያየት በአሸባሪነት ከተፈረጀው የህወሓት ድርጅት ጋር ምንም ዓይነት ድርድር እንደማይኖር ገልፀዋል።

ሆኖም ግን በፌደራል መንግሥት የታሰበው ህዝባዊ መግባባትን የመፍጠር የውይይትና የምክክር መድረክ እጅግ ጠቃሚ መሆኑን፣ ለዴሞክራሲ ግንባታ እና ለሀገር ቀጣይነትም አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።

በምክክር መድረኩ ላይ ሁሉም የክልሉ ህዝብ ተሳታፊ እንደሚሆን ጠቅሰው የተከፈለው ዋጋ ቀላል ባለመሆኑ ከአሸባሪው ህወሓት ጋር ምንም ዓይነት ድርድር እንደማይኖር አንስተዋል።

አገልግሎት አቋርጠው የነበሩ ሁሉም የመንግሥት ተቋማት ወደ ሥራ እንደሚገቡም የአማራ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ መግለፃቸውን ኢቢሲ ዘግቧል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.