Fana: At a Speed of Life!

ኢ/ር ታከለ በመዲናዋ ተከራዮች በነፃ እንዲገለገሉ ለፈቀዱ አከራዮች ምስጋና አቀረቡ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 30፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ አከራዮች አቅም ለሌላቸውና አነስተኛ ንግድ ለሚሰሩ ወገኖች የእፎይታ ጊዜ እንዲሰጧቸው ጥሪ አቅርበዋል።

ይህንን ተከትሎም በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ አከራዮች ፈጣን ምላሽ እየሰጡ ይገኘሉ።

በዚህም የገበያ ማዕከላት እና የመኖሪያ ቤት አከራዮች ተከራዮቻቸው ለሁለት እና ሶስት ወራት በነፃ እንዲገለገሉ ፈቅደዋል።

ኢንጂነር ታከለ ኡማም ያቀረቡትን ጥሪ ተከትሎ ይህንን ውሳኔ ለወሰኑ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

ሌሎች አከራዮችም የእነዚህን ፈለግ እንደሚከተሉ ባለሙሉ ተስፋ ነኝ ብለዋል።

በሀዋሳ ከተማ የሚገኘው የሀዋሳ ግራንድ ሞል ባለቤትም ህንፃውን ለተከራዮ ነጋዴዎች የሁለት ወር ኪራይ ነፃ አድርገዋል ተብሏል።

በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ የነጋዴዎች የገቢ መጠን ስለሚቀንስና በዚህም ምክንያት ሰራተኞቻቸውን ለመቀነስ ሊገደዱ ስለሚችሉ ያ እንዳይሆን ቢያንስ የኪራይ ወጪያቸውን በመቀነስ አጋርነታቸውን ለማሳየት ይህንን መልካም ተግባር ማከናወናቸውን ተናግረዋል።

“ሁላችንም በመተጋገዝና በመረዳዳት ይህንን ጊዜ ማለፍ አለብን” ያሉት ወ/ሮ አማረች ችግሩ እስኪወገድ ድረስ እየተጋገዝንና እየተማከርን እንዘልቃለን ብለዋል።

ወ/ሮ አማረች በተጨማሪም ለሃዋሳ ከተማ አስተዳድር ለኮሮና ቫይረስ ስርጭት መግቻ ስራ እንዲሆን የ150 ሺህ ብር ስጦታ አበርክተዋል።

የሃዋሳ ሴንትራል ሆቴል እና የግራንድ ሞሉ ባለቤት ወሮ አማረች አያይዘውም በተቻለ መጠን ከከተማው አስተዳደር ጎን እንደሚቆሙ ቃል ገብተዋል።

በሆቴሉ የሚገኙ ሰራተኞቻቸውም ምንም እንኳን ስራ ባይኖርም ሳይበትኑ ችግሩ መፍትሄ እስኪያገኝ ድረስ አብረዋቸው እንደሚሆኑ ተናግረዋል።

ኅብረተሰቡም በዚህ የጋራ ኅብረት በሚያስፈልግበት ጊዜ በመተጋገዝ እና በመተሳሰብ አብሮ እንዲሆን መክረዋል።

ከሁሉም በፊት ጤና ቀዳሚ በመሆኑ ኅብረተሰቡ የጤና ባለሙያዎች የሚሰጡትን ቅድመ ጥንቃቄ ተግባራዊ በማድረግ ከቫይረሱ እራሱንና ወገኑን ይጠብቅ ሲሉ መክረዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.