Fana: At a Speed of Life!

ኮቪድ19 አሜሪካን 16 ትሪሊየን ዶላር ሊያሳጣት እንደሚችል የሃገሪቱ የቀድሞ የግምጃ ቤት ሃላፊ አስታወቁ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 3 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ኮቪድ19 አሜሪካን 16 ትሪሊየን ዶላር ሊያሳጣት እንደሚችል የሃገሪቱ የቀድሞ ከፍተኛ ባለስልጣን ተናገሩ፡፡

የቀድሞው የአሜሪካ የግምጃ ቤት ሃላፊ ላውረንስ ሳመርስ እና የሃርቫርድ ዪኒቨርሲቲው የምጣኔ ሃብት ምሁር ዴቪድ ከትለር ዋሽንግተን በኮቪድ19 ምክንያት ከጠቅላላ የሃገር ውስጥ ምርት እድገቷ ውስጥ ወደ 90 በመቶውን ልታጣ ትችላለችም ብለዋል፡፡

ከዚህ ውስጥ ግማሹ በቫይረሱ ሳቢያ በተቀዛቀዘው ኢኮኖሚ የምታጣው ሲሆን ቀሪው ደግሞ ለጤና እና መሰል መደጎሚያዎች የምታውለው መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

ሃገሪቱ ታጣዋለች የተባለው ገንዘብ አጋጥሟት ከነበረው የኢኮኖሚ ድቀት በአራት እጥፍ ሊልቅ ይችላልም ነው ያሉት፡፡

ከዚህ ባለፈም ከፈረንጆቹ 2011 ጀምሮ በአፍጋኒስታን፣ ኢራቅ እና ሶሪያ ባካሄደቻቸው ጦርነቶች ካወጣችው ወጪ በሁለት እጥፍ የበለጠ እንደሚሆንም አስረድተዋል፡፡

የቀድሞው የግምጃ ቤት ሃላፊ እና የምጣኔ ሃብት ባለሙያ እንደሚሉት በኮቪድ19 ምክንያት የተጎዳው ኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን የዜጎች ህልፈትና የኑሮ ደረጃ መቀነስም ከኢኮኖሚ አንጻር ይታያል፡፡

በዚህም በአሜሪካ ሊሰሩ የሚችሉ ዜጎች ያለጊዜ ለህልፈት መዳረግ በቀጣዩ አመት በኢኮኖሚው ላይ የ4 ነጥብ 4 ትሪሊየን ዶላር የሚገመት ዋጋ እንደሚኖረውም ያስረዳሉ፡፡

ይህ ደግሞ የሃገሪቱ መንግስት የዜጎችን ጤንነት ለመጠበቅና የተጎዳውን ኢኮኖሚ ለመደጎም ከሚያወጣው ገንዘብ ጋር ተዳምሮ ሃገሪቱን ለከፍተኛ ኪሳራ ይዳርጋታልም ነው ያሉት በአሜሪካ የህክምና ማህበር ገጽ ላይ ባሰፈሩት ፅሁፍ፡፡

አሜሪካ ዓለም ላይ በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ ክፉኛ ከተጠቁ ሃገራት መካከል ቀዳሚዋ ናት፡፡

በትናንትናው እለት ብቻ ከ7 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ሲገኝባቸው ከ214 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ ለህልፈት ተዳርገዋል ተብሏል፡፡

ምንጭ፥ ሺንዋ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.