Fana: At a Speed of Life!

የህብረቱ መሪ ሀሳብ የአፍሪካን ወቅታዊ ሁኔታ ያገናዘበ ነው – አቶ ነቢያት ጌታቸው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 6፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ መሪ ሀሳብ የአፍሪካን ወቅታዊ ሁኔታ ያገናዘበ፣ተገቢና በአፍሪካ ሰላም እስከሚሰፍን ድረስ መተግበር ያለበት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነቢያት ጌታቸው አስታወቁ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነቢያት ጌታቸው በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም ‘’የመሳሪያ ድምፅ የማይሰማባትን አህጉር በመፍጠር ለአፍሪካ ልማት ምቹ ሁኔታ መፍጠር’’ የሚለው የህብረቱ መሪ ሀሳብ በአፍሪካ ሰላም እስከሚሰፍን ድረስ መተግበር ያለበት ነው ብለዋል፡፡

ስለሆነም በአፍሪካ ግጭትና ጦርነትን ለማስወገድ የግጭቶቹን መሰረታዊ መንስኤ በመለየት እልባት መስጠት እንደሚያስፈልግና ለጊዜው ጦርነትንና ግጭቶችን ለመከላከል መሪ ሀሳቡን ተፈጻሚ ማድረግ ጠቃሚ መሆኑን ኢትዮጵያ ማሳወቋን ገልጸዋል።

ከዚህ ባሻገር በጉባኤው ኢትዮጵያ በአህጉራዊና በዓለም አቀፍ ደረጃ የምታካሂዳቸው የምርጫ ውድድሮች የተሳኩ እንዲሆኑ ሰፊ የማግባባት እና የማሳመን ስራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል፡፡

እንዲሁም ኢትዮጵያ ለሁለት የህብረቱ ተቋማት፣ ለአፍሪካ ህብረት የሰላምና ጸጥታ ምክር ቤት እና ለአፍሪካ ህብረት የታዋቂ ሰዎች ፓነል መመረጧን ተናግረዋል፡፡

አቶ ነቢያት አያይዘውም ኢትዮጵያ አፍሪካን በመወከል ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚቴና በድርጅቱ የህጻናት መብት ኮሚቴ መመረጥ መቻሏን አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ጎን ለጎን የናይጄሪያውን ፕሬዚዳንት መሀሙዱ ቡሀሪን፣ የኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ቱሩዶን ይፋዊ የስራ ጉብኝት ማስተናገዷም ተናግረዋል።

እንዲሁም ከሌሎች ሀገራት መሪዎች ጋር የሁለትዮሽ ውይይት መካሄዱን አብራርተዋል።

ከዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ አንጻርም 128 እስረኞ ከታንዛኒያ እስር ቤቶች ተፈተው በዛሬው ዕለት ሀገራቸው እንደሚገቡ እንዲሁም በቻይና የሚማሩ ኢትዮጵያውያን በኮሮና ቫይረስ እንዳይጠቁ አስፈላጊው ክትትል እየተደረገ እንደሆነም ነው ቃል አቀባዩ የተናገሩት፡፡

ቃል አቀባዩ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ ከየካቲት 9 እስከ 11 ቀን 2012 ዓ.ም በኢትዮጵያ ጉብኝት እንደሚያደርጉ መግለጻቸውንም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.