Fana: At a Speed of Life!

የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በአቶ ልደቱ አያሌው እጅ የተገኘውን ሽጉጥ እንዳላስታጠቃቸው መርማሪ ፖሊስ ገለፀ

አዲስ አበባ ፣ ነሀሴ 11 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በአቶ ልደቱ አያሌው እጅ የተገኘው አንደኛውን ሽጉጥ እንዳላስታጠቃቸው እና ሽጉጡ ኢሳያስ ወልደጊዮርጊስ በተባለ ሰው ስም የተመዘገበ ነው ሲል ምላሽ መስጠቱን መርማሪ ፖሊስ ገለፀ።
 
ዛሬ ለሶስተኛ ጊዜ በቢሾፍቱ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት የቀረቡት አቶ ልደቱ አያሌው አቶ ኢሳያስ በወቅቱ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ምክትል ሀላፊ እንደነበሩ ጠቅሰዋል።
 
ይሁንና እሳቸው ኃላፊነታቸውን ተጠቅመው የሰጧቸው መሆኑን ያብራሩ ቢሆንም መርማሪ ፖሊስ ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ያቀረበው ማስረጃ ግን ተቋሙ ያስታጠቃቸው እንዳልሆነ ተመልክቷል።
 
ፍርድ ቤቱ በባለፈው ቀጠሮ በሀገር ውስጥ የልብ ህክምና እንዲያገኙ አዞ የነበረ ሲሆን፥ አቶ ልደቱ ላንድ ማርክ ሆስፒታል ክትትል ማድረጋቸውን እና የልብ እና የአስም ህመምተኛ መሆናቸውን የህክምና ማስረጃ በፅሁፍ አያይዘው አቅርበዋል።
 
ፍርድ ቤቱም ይህን ተረድቶ ወደውጭ ሀገር ተጉዘው እንዲታከሙ እንዲፈቅድላቸው፥ እንዲሁም የታሰሩበት እስር ቤት ለበሽታ ተጋላጭ እንደሚያደርጋቸው እና የጤናቸው ሁኔታ አደጋ ውስጥ እንደሆነ በመጥቀስ በዋስ እንዲፈቱ ጠይቀዋል።
 
አቶ ልደቱ ከዚህ በፊት በቀረቡበት ጊዜ ጥብቅና የሚቆምላቸው ሰው ማጣታቸውን መግለፃቸውን ተከትሎ ፍርድ ቤቱ ህገመንግስታዊ መብታቸው እንዲከበር በማሰብ የመንግስት ተከላካይ ጠበቃ አቁሞላቸዋል።
 
መርማሪ ፖሊስ ባቀረቡት የዋስትና ጥያቄ ላይ በርካታ ምርመራ እየሰራ መሆኑን ገልፆ በእጃቸው ላይ የተገኘ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ፎረንሲክ ምርመራ መላኩን እና ውጤት እየተጠባበቀ መሆኑን በመግለፅ የጀመረውን የምርመራ ስራ አጠናቆ እንዲቀርብ ተጨማሪ የ14 ቀን ይሰጠኝ ሲል ፍርድ ቤቱን ጠይቋል ።
 
ጉዳዩን የተከታተለው ፍርድ ቤቱም የጤናቸውን ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያስገባ ምቹ አያያዝ እንዲኖር ለፖሊስ ትእዛዝ ሰጥቷል።
 
ጤናቸውንም በተገቢው መልኩ በሀገር ውስጥ እንዲከታተሉ ትእዛዝ በመስጠት መርማሪ ፖሊስ ምርመራውን አጠናቆ እንዲቀርብ ተጨማሪ ሰባት ቀን ሰጥቶታል።
 
 
በታሪክ አዱኛ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.