Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ ዝግጅትና ትግበራ ተሞክሮ በትምህርት ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ጥር 13፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ ዝግጅትና ትግበራ ተሞክሮ በትምህርት ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ መቅረቡን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ኘሮፌሰር ሂሩት ወልደማሪያም የተመራ ልዑክ በለንደን እየተካሄደ ባለው የትምህርት ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ ተሳትፏል።

በመድረኩም ኢትዮጵያ የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ ዝግጅትና ትግበራ አካሄዷን እንድታቀርብ ተመርጣ በፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም አማካኝነት አቅርባለች።

በዚህም ፍኖተ ካርታው የሌሎች ሃገራት ተሞክሮ ላይ ጊዜ ወስዶ ጥናት መጠናቱና መዘጋጀቱ፣ የመንግሥት ቁርጠኝነት፣ ከ3 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ህዝብ በውይይት ማሳተፍ መቻሉ፣ 13 መሠረታዊ የለውጥ ሃሳቦች መለየታቸው እና የተግባር እቅድ መዘጋጀቱ፥ በተሳታፊዎች ዘንድ አድናቆት እንዲቸረው ማድረጉ ተጠቅሷል።

ጉባኤው በየአመቱ ጥር ወር ላይ በለንደን ከተማ የሚካሄድ የትምህርት ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት መሆኑም ተገልጿል።

በጉባኤው ላይ የ130 ሀገራት ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ዲኤታዎች፣ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ የትምህርት ኃላፊዎች፣ በትምህርት ላይ የሚሰሩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን ጨምሮ የሲቪክ ማህበራት እየተሳተፉ መሆኑን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.