Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮ ቴሌኮምን ከ5 ሚሊየን ብር በላይ ያሳጣው ተከሳሽ በጽኑ እስራት ተቀጣ

አዲስ አበባ፣ ጥር 20፣ 2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) በህገ-ወጥ መንገድ ዓለም አቀፍ ጥሪ በማስተላለፍ ኢትዮ ቴሌኮምን ከ5 ሚሊየን ብር በላይ እንዲያጣ ያደረገው ተከሳሽ በ9 ዓመት ጽኑ እስራትና ገንዘብ ተቀጣ፡፡

ተከሳሹ የቴሌኮም መሳሪያዎችን ወደ ሀገር ዉስጥ በማስገባት፣ በመጠቀም እና የቴሌኮም አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ሕጋዊ ፈቃድ ሳይኖረው በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 ከግለሰብ ቤት በመከራየት ሲሠራ መቆየቱ ተገልጿል፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም ሲም ካርዶችን በውስጣቸው በማስገባት በአንድ ጊዜ ብዛት ያላቸውን ጥሪዎች በቅናሽ በማስተላለፍ ከመጋቢት 30 ቀን 2010 እስከ ጳጉሜን 1 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ መስራቱ ተመላክቷል፡፡

በዚህ ጊዜ ውስጥ ከውጭ ሀገር ወደ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የስልክ ጥሪዎችን በማስተላለፍ ኢትዮ ቴሌኮም ያገኝ የነበረዉን 5 ሚሊየን ብር እንዲያጣ በማድረጉ በወንጀል መከሰሱ ተገልጿል፡፡

ዓቃቤ ሕግ ተከሳሽ በፈፀመው ወንጀል ተጠያቂ እንዲሆን የሰው ምስክሮች፣ የሰነድ እና የኤግዚቢት ማስረጃዎችን ለፍርድ ቤቱ በማቅረብ ተከራክሯል፡፡

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 12ኛ የወንጀል ችሎት መዝገቡን መርምሮ ተከሳሽን በፈፀመው ወንጀል ጥፋተኛ በማለት በ9 ዓመት ጽኑ እስራትና በ45 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ መወሰኑን ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.