Fana: At a Speed of Life!

የኮሮና ቫይረስ መከላከያ መንገዶችን በጥንቃቄ በመተግበር ተቋርጦ የቆየውን ትምህርት ለማስጀመር ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን የኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች አስታወቁ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 13 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኮሮና ቫይረስ መከላከያ መንገዶችን በጥንቃቄ በመተግበር ተቋርጦ የቆየውን ትምህርት ለማስጀመር ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን የኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች ትምህርት ቢሮዎች አስታውቀዋል፡፡

የክልሎቹ ትምህርት ቢሮዎች ተማሪዎች በክፍል ውስጥ የሚኖራቸውን አካላዊ ርቀት ለመጠበቅ አዳዲስ ትምህርት ቤቶችን በመገንባትና፤ ተማሪዎችን በፈረቃ ለመቀበል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ገልጸዋል።

የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ኤፍሬም ተሰማ እንደገለጹት፣ የክልሉ ተማሪዎች በኮሮና ቫይረስ ዙሪያ ያላቸውን ግንዛቤ ለመጨመር በመገናኛ ብዙሃን እና በተለያዩ መንገዶች ሲሰራ ቆይቷል።

አሁን ላይ የኮሮና ቫይረስ መከላከያ መንገዶችን ግምት ውስጥ በማስገባት የ2013 ትምህርት ዘመንን ለማስጀመር በርካታ ዝግጅቶች ተደርገዋል ነው ያሉት ።

ተማሪዎች በክፍል ውስጥ ርቀታቸውን ጠብቀው እንዲማሩ በመንግስት እና በህብረተሰቡ ተሳትፎ ተጨማሪ ከ32 ሺህ በላይ አዳዲስ መማሪያ ክፍሎች መሰራታቸውንም ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም በክልሉ ትምህርት ቤቶች የሚስተዋለውን የመጸዳጃ ቤት እጥረት ለመቅረፍ ደረጃቸውን የጠበቁ 8 ሺህ 194 መጸዳጃ ቤቶች ለአገልግሎት ዝግጁ ሆነዋል።

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ይልቃል ከፋለ በበኩላቸው የኮሮና ቫይረስ መከላክያ መንገዶችን ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ፤ ትምህርት ለማስጀመር የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ ተማሪዎች በክፍል ውስጥ የሚኖራቸውን ጥግግት እና ንክኪ ለማስወገድ የተሰሩት መማሪያ ክፍሎች በቂ አለመሆናቸውን የገለጹት ሃላፊው፣ ይህንን ችግር ለማስወገድም ተማሪዎችን በሶስት ፈረቃ ለማስተማር ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚያጋጥመውን የመምህራን አጥረት ለመቅረፍም ተጨማሪ የሰው ሃይል የማሟላት ስራ ይከናወናል ያሉት ቢሮ ሃላፊው ፤መምህራንም ችግሩን ግምት ውስጥ በማስገባት ልክ እንደ ህክምና ባለሞያዎች ሁሉ ሀገራዊ ሃላፊነታቸውን እንደሚወጡ እምነታቸው መሆኑን አንስተዋል።

የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብልን እንዲሁም የሙቀት መለኪያን ከቅድመ መደበኛ ተማሪዎች ጀምሮ በመንግስት ደረጃ ለማቅረብ ዝግጅት እየተደረገ ብለዋል።

ውሃ በሌለባቸው ትምህርት ቤቶችም ችግሩ እስኪስተካከል ድረስ ተማሪዎች ለንፅህና መጠበቂያም ሆነ ለመጠጥ አገልግሎት የሚውል ውሃ ይዘው መሄድ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።

የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ መከሰቱን ተከትሎ ከ42 ሺህ በላይ በሚሆኑ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩ ከ26 ሚሊየን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ሆነው ቆይተዋል።

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.